ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ 12ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀን 7፡00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል፡፡
ፋሲል ከነማ 21 ነጥብ በመያዝ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በ11ኛው ሳምንት ከባሕር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት አፄዎቹ እስከ 11ኛው ሳምንት ድረስ በአንድም ጨዋታ አለመሸነፋቸው ቡድኑ ጠንካራ ስለመኾኑ ማሳያ ነው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ፋሲል ከነማ ያለመሸነፍ ጉዞውን ቢያስቀጥልም በአምስት ጨዋታዎች አቻ መለያየቱ ግን የአጥቂው ክፍል ጥያቄ ይነሳበታል። በፋሲል ከነማ በኩል አምስት ያህል ተጫዋቾች በቅጣት እና በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አይሰለፉም ተብሏል፡፡
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ ፋሲል ከነማን ካሸነፈ ደረጃውን ከፍ ማድረግ ያስችለዋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ በዘጠኝ ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ ፋሲል ከነማ በአምስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በሦሥት ጨዋታዎች ድል አድርጓል፡፡ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል ከነማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ሲዳማ ቡና እስኪጫወት ድረስ ሊጉን ይመራል።
ባሕር ዳር ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቀን 10፡00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታል፡፡ ባሕር ዳር ከተማ በ14 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
ቡድኑ ኢትዮጵያ መድንን ካሸነፈበት የስምንተኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ድል ማድረግ አልቻለም፡፡የአጥቂው ክፍል ከነበረበት ግብ የማሰቆጠር ድርቅ ወጥቶ ግብ በማስቆጠር የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃውን የሚያሻሽል ይኾናል፡፡በባሕር ዳር ከተማ በኩል ሙሉ ሥብሥቡ ለጨዋታው ብቁ ነው ተብሏል፡፡
ተጋጣሚው ውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስምንት ነጥብ ብቻ በመያዝ ወራጅ ቀጣና ላይ ተቀምጧል፡፡ ዛሬ ከወራጅ ቀጣና ስጋት የሚያስወጣውን ድል ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጨዋታዎች ተገናኝተው ባሕር ዳር ከተማ በሁለት ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአንድ ጨዋታ አሸንፏል፡፡ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ቀን 9፡00 ወላይታ ዲቻ ከአርባምንጭ ከነማ ይጫወታሉ። መቀለ 70 እንደርታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምሽት 12፡00 በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ ሲል ያስነበበው ኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



