ዛሬ በሚደረጉ አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ማን ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላል ?

0
50
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ምድብ ሁለት ላይ የሚገኙት አንጎላ ከግብጽ፣ ዚምባብዌ ከደቡብ አፍሪካ ምሽት1:00 ይጫወታሉ።
አንጎላ እና ግብጽ በታሪክ በስምንት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው። ግብጽ በአራት ጨዋታዎች አንጎላን አሸንፋለች። በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ግብጽ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና ሁለት የግብ ክፍያ በመያዝ በስድስት ነጥብ ምድቡን በመምራት ላይ ትገኛለች።
ፈርዖኖቹ (ግብጽ) የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ የምድብ ጨዋታዎችን ሁሉም በማሸነፍ በበላይነት ያጠናቅቃሉ።
የግብጽ ተጋጣሚ አንጎላ በአንድ ጨዋታ ተሸንፋ እና በአንድ ጨዋታ አቻ በመለያዬት አንድ ነጥብ እና አንድ የግብ ዕዳ ይዛ በሦሥተኛነት ተቀምጣለች።
አንጎላ ጨዋታውን ብታሸንፍ እንኳ ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ ሰዓት ከዚምባብዌ የምታደርገውን ጨዋታ ካልተሸነፈች ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል አጣብቂኝ ውስጥ የምትገባ ይኾናል።
በታሪክ አንጎላ ግብጽን በእግር ኳስ አሸንፋ አታውቅም። ዛሬስ? በስታዲ ደ አጋዲር የሚደረገው ጨዋታ ምላሹን ይሰጣል።
በዚሁ ምድብ ዚምባብዌ ከደቡብ አፍሪካ ምሽት 1:00 በስታዲ ዴ’ማራካሽ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ኾኗል።
ሁለቱ ሀገራት በታሪክ በ19 ጨዋታ ተገናኝተዋል።
ደቡብ አፍሪካ ዚምባብዌን በስምንት ጨዋታዎች አሸንፋለች። ዚምባብዌ ደግሞ በስድስት ጨዋታዎች ድል አድርጋለች። በአምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሞሮኮ እያስተናገደችው ባለው የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፋ በአንዱ ደግሞ ተሸንፋ ሦሥት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት።
ዚምባብዌ በበኩሏ በአንድ ጨዋታ አቻ በመውጣት እና በአንዱ በመሸነፍ አንድ ነጥብ እና አንድ የግብ ዕዳ በመያዝ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ተቀምጣለች። ደቡብ አፍሪካ ጨዋታውን ካሸነፈች በቀጥታ ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች።
ምድብ አንድ ላይ ደግሞ ኮሞሮስ ከማሊ፤ ዛምቢያ ከሞሮኮ ምሽት 4:00 ወሳኝ የምድብ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኮሞሮስ እና ማሊ እስካሁን በሁለት ጨዋታዎች እርስ በእርስ ተጫውተው ማሊ በሁለቱም አሸንፋለች።
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ ማሊ በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ በመለያዬት ሁለት ነጥብ አላት።
ኮሞሮስ በበኩሏ በአንድ ጨዋታ ተሸንፋ እና በአንድ ጨዋታ አቻ በመለያዬት ያላት ነጥብ አንድ ብቻ ነው።
በጨዋታው ሞሮኮ ዛምቢያን ብታሸንፍ እና ኮሞሮስ ማሊን ድል ካደረገች ከምድቡ ግርጌ ያለችው ኮሞሮስ ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች።
ዛምቢያ እና ሞሮኮ ምሽት ይጫወታሉ። ሁለቱ ሀገራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ በዘጠኝ ጨዋታዎች ተገናኝተው ሞሮኮ በሰባቱ ስታሸንፍ ዛምቢያ ድል ያደረገችው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው።
ሞሮኮ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ በአንዱ አሸንፋ እና በአንዱ አቻ ተለያይታ አራት ነጥብ በመያዝ ምድቡን እየመራች ትገኛለች።
ዛምቢያ ደግሞ እስካሁን ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች አቻ በመለያዬት በሁለት ነጥብ ሦሥተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ዛሬ የሚደረጉ ጨዋታዎች ወደ ጥሎ ማለፉ የሚቀላቀሉ እና ከውድድሩ የሚሰናበቱ ሀገራትን ያሳዩናል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here