የዲያጎ ጆታ ልጆች በአንፊልድ

0
83
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከሊቨርፑል ጋር ዋንጫን ያሳካው ፖርቱጋላዊው ዲያጎ ጆታ በመኪና አደጋ ሕይዎቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
በአንፊልድ በሚደረጉ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የቀዮቹ ደጋፊዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ውድ አጥቂያቸውን እያስታወሱት ይገኛሉ፡፡ 20 ቁጥር የጆታ መለያ ቁጥር መኾኑም አይዘነጋም፡፡
ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል ከዎልቭስ ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ የቀዮቹ ደጋፊዎች በ20ኛው ደቂቃ ጆታን ከማሰብ የዘለለ ነገር እንደሚጠብቃቸው ፖል ጆይስ በትዊተር ገጹ አስነብቧል፡፡
ዲያጎ ጆታ ከወልቭስ ወደ ሊቨርፑል አምርቶ በሊቨርፑል ስኬታማ ዓመታትን ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡ ቅዳሜ በአንፊልድ ዎልቭስ እና ሊቨርፑል ሲገናኙም ደጋፊዎች የጋራ ልጃቸውን በጋራ የሚያስታውሱት ይኾናል፡፡
በአንፊልድ በሚካሄደው የ19ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ የዲያጎ ጆታ ልጆች የኾኑት ዴኒስ እና ዱአርቴ ጆታ በተጨዋቾች እጃቸው ተይዞ (ማስኮት) ኾነው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡
ይህ ክስተት የዎልቭስ እና የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ቀልብ ይስባል ተብሎ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ከወንድሙ ጋር ሕይዎቱ ያለፈው ዲያጎ ጆታ ልጆቹ በአንፊልድ “ዩ ኔቨር ዎክ አሎን” (ብቻችሁን አይደላችሁም) በሚለው ዝማሬ ታጅበው የማይረሳውን አባታቸውን በክብር ያስታውሱታል፡፡
ዓመታዊውን የጆታን ደመወዝ ለቤተሰቦቹ ከመክፈል ጀምሮ በአንፊልድ ዓመቱን ሙሉ በ20ኛው ደቂቃ ጆታን የሚያስቡት የቀዮቹ ኀላፊዎች እና ደጋፊዎች ቅዳሜ ደግሞ የውድ ልጃቸውን ልጆች ወደ ሜዳ አስገብተው የሚያጽናኑበት መንገድ ከወዲሁ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here