እኛም አለን ትዝታ!

0
14
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በሞሮኮ ይጀመራል። ለቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታትም አፍሪካዊነት በእግር ኳስ ይደምቃል።
አሁን ላይ 24 ሀገራትን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ውድድሩ እውን እንዲኾን ባለውለታ ከሚባሉ ሀገራት መካከል የኾነችው ኢትዮጵያን አያሳትፍም።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገራት ናቸው። አሁን ላይ ግብጽ እንደ ውድድሩ መስራች ሀገር እግር ኳሷ በልኩ አድጎ በአፍሪካ ዋንጫ የገዘፈ ታሪክ ባለቤት ናት።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ እና ሱዳን “የፊተኞች የኋላ ይኾናሉ” አይነት እርግማን በመሰረቱት ውድድር ለመሳተፍ እንኳ ሲቸገሩ መመልከት የተለመደ ነው።
በተለይ ለአፍሪካ እግር ኳስ በአደረጉት አስተዋጽኦ “የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት” በሚል የሚጠሩት የይደነቃቸው ተሰማ ሀገሯ ኢትዮጵያ የእግር ኳሷ የቁልቁለት ጉዞ አሁንም አስጊ ነው።
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሰዓታት በኋላ በሞሮኮ በድምቀት ይጀመራል። ምክንያታችን ይሄ ኾኖ ወዲህ ደግሞ ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን እኛም አለን ትዝታ እንላለን።
ጊዜው 1954 ዓ.ም ነው። ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ ተደግሷል። አንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሱዳን እና ግብጽ ተከናውኖ ግብጽ አሸናፊ ኾናለች።
ሦስተኛው ዋንጫ በአዲስ አበባ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም ሲካሄድ ኢትዮጵያ አዘጋጅ በመኾኗ፣ ግብጽ ደግሞ ያለፈውን ዋንጫ ባለድል በመኾኗ ማጣሪያ ሳያደርጉ በቀጥታ አለፉ።
ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ ማጣሪያ አደረጉ። ቱኒዚያ እና ኡጋንዳ ማጣሪያውን አልፈው ኢትዮጵያ እና ግብጽን ተቀላቀሉ። አራቱ ቡድኖች በዕጣ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ እና ግብጽ ከኡጋንዳ ተመደቡ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ቀደም ብሎ ጀምሯል። በወዳጅነት ጨዋታ ኬንያን 4ለ3 እና 6ለ1 በማሸነፍ ጥሩ ወኔ ላይ ነው።
ጥር 6/1954 ዓ.ም ለዋንጫ ለመድረስ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ ተጫወቱ። የደጋፊው ስሜት የተለየ ነበር። ምክንያቱም ባለፉት ዋንጫዎች ብሔራዊ ቡድኑ ከመሳተፍ ውጭ ድል አላስመዘገበም። አሁን ይሄ ታሪክ መቀየር አለበትና ነው።
በጨዋታው ኢትዮጵያ 4ለ2 አሸነፈች። በዚያ በኩል ደግሞ ግብጽ እና ኡጋንዳ ተጫወቱ እና ግብጽ አሸነፈች። ለዋንጫ ኢትዮጵያ ከግብጽ ተፋጠጡ።
አዲስ አበባ ሀሳቧ ለሁለት ተከፈለ። አንዱ የግብጽ ማለፍን እንደመጥፎ እድል ቆጠረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽ በአንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ ላይ ለወሰደችው የበላይነት ጥሩ የበቀል ጊዜ ነው ተባለ።
ጥር 13/1954 ዓ.ም ብዙ የተወራለት፣ ብዙ የተመከረበት እና ብዙዎች እንቅልፍ ያጡለት የዋንጫ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከግብጽ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም።
ስታዲየም ውስጥ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ ሜዳው የጠጠር መጣያ የለውም። ጨዋታው ተጀመረ። ሜዳው ውስጥ እልህ እና ፍርሃት ይታያል።
የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በአንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሱዳን እና ኢትዮጵያን በሰፊ ግብ እያሸነፈ የዋንጫ ባለቤት ኾኗል። ይሄ ለብዙዎች ፍርሃት ፈጥሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የማይነካ የመሰለውን የግብጽ ቡድን አንገት ለማስደፋት ወኔ የፈነቀለው ብዙ ነው።
ጨዋታው ተጀምሮ ብዙ ደቂቃ ሳይጓዝ ግብጾች አገቡ፣ የሞቀው ስታዲየም ድባብ ጸጥ አለ። የመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ።
ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ ተመልካቹ እንዲህ አለ” መሸነፍ አይቻልም፤ አዎ በግብጽ መሸነፍ ያመናል”
ውጥረቱ ጣሪያ የነካው ሁለተኛ የጨዋታ ጊዜ ተጀመረ ኢትዮጵያ በተክሌ (ወዲ ቀጭን) አማካኝነት አቻ ኾነች። አዲስ አበባ በአንድ እግሯ ቀመች። ግን የግብ ቀበኛው መሐመድ በዳዊ ወዲያው ግብጽን መሪ አደረገ። ቢኾንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጭኖ መጫወት ጀመረ።
ደቂቃው እየነጎደ ነው ስታዲየሙ ለግብጾች እሳት፣ ለኢትዮጵያውያን ብርታት ኾኖ ቀጠለ። “በግብጽ መሸነፍ ያመናል” በሜዳው አራቱም አቅጣጫ ከፍ ብሎ ይሠማል።
በመጨረሻ ሉቻኖ ቫሳሎ ኢትዮጵያን ከጉድ ታደገ። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ግብ አስቆጠረ። በደስታ የተቃቀፈ፣ ያለቀሰ፣ ይይዘው ይጨብጠውን ያጣውን ቤት ይቁጠረው።
ጨዋታው በጭማሪ ሰዓት ሲቀጥል ግብጾች ጉልበታቸው ራደ። መንግሥቱ ወርቁ፣ ቫሳሎ እና ኢታሎ ቫሳሎ ለግብጽ ተከላካዮች ፈተና ኾኑ።
ኢታሎ ሦስተኛውን፣ መንግሥቱ ደግሞ አራተኛውን ግብ አከታትለው አስቆጠሩ። ጨዋታው 4ለ2 ተጠናቀቀ። አምበሉ ሉቺያኖ ዋንጫውን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ተቀበለ።
አያ ሆሆሆ…ማታ ነው ድሌ ከስታዲየም አልፎ ምሽቱን ሙሉ በአዲስ አበባ ሲደለቅ ማምሸቱን የቆዩ የጋዜጣ ጹሑፎች እና በተለያየ ጊዜ የተላለፉ የራዲዮ ዝግጅቶች እማኝ ናቸው።
ወዲህ ለሀበሻ ምድር በአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛው ድል ይህ የእነ መንግሥቱ ወርቁ እና የቫሳሎዎች ገድል ኾኖ እስካሁን ተቀምጧል። አዎ እኛም አለን ትዝታ!
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here