“የቡድኑ አባላት የማሸነፍ ሥነ ልቦና ላይ ናቸው” ባሕር ዳር ከተማ ሥራ አሥኪያጅ

0
58
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ባሕር ዳር ከተማ ከምድረ ገነት ሽረ ጋር ቀን 9:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫዎታል፡፡
የጣናው ሞገድ በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ ማግኘት ከነበረበት 27 ነጥብ 12 ነጥብ በማያዝ ያለምንም የግብ ክፍያ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ቡድኑ በሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 አሸንፏል፡፡ ይሁንና የጣናው ሞገድ የማሸነፍ ተነሳሽነቱን በወጥነት ማስቀጠል አልቻለም፡፡
መገለጫዎቹ ደግሞ በሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር በሸገር ከተማ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ ደግሞ በቦዲቲ ከተማ ተሸንፎ ከፉክክሩ ውጭ ኾኗል፡፡
“ለምን?”    የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድን ሥራ አሥኪያጅ ልዑል ፍቃዱ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ በሰጡት አስተያየት ቡድኑ ለወጣቶች ዕድል ሰጥቶ ማጫወቱን በመልካምነት አንስተዋል፡፡
አራት ያህል የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ይህም ለተከታታይ ሽንፈት ዳርጎናል ብለዋል፡፡
ሥራ አሥኪያጁ አክለውም ቡድኑ ከሃዋሳ ጨዋታ መልስ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ከተማ አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ ተጫዋቾችም በጥሩ ሁኔታ ሥልጠናቸውን እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ የቡድኑ አባላት ከቁዘማ ወጥተውም የማሸነፍ ሥነ ልቦናቸው መልካም መኾኑን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
የቡድኑ የተከላካይ እና የአማካይ ክፍሉ ጠንካራ ነው፤ ጉዳት ላይ የቆዩ ወሳኝ የአጥቂ ባሕርይ ያላቸው ተጫዋቾችም ዛሬ ወደ ጨዋታው ይመለሳሉ፡፡ በመኾኑም በዛሬው ጨዋታ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ስለሚሰለፉ ውጤታማ ጨዋታ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃን ከፍ የሚያደርግ ይኾናል፡፡ ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽረ በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ 13 ነጥብ እና ሁለት ንጹሕ የግብ ክፍያ በመያዝ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባ ምንጭ ከተማ ይጫወታሉ፡፡ ምሽት 12 ሰዓት ግሞ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መቀሌ 70 እንደርታ ከሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here