ወንድማማቾች በአፍሪካ ዋንጫ

0
78
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ታሕሣሥ 12/2018 ዓ.ም ይጀመራል፡፡
በዚህ ውድድር በርካታ አስገራሚ ነገሮችን እንደምንመለከት ተስፋ እያደረግን ለአሁኑ ባለፉት የአፍሪካ ዋንጫዎች በጋራ ለሀገራቸው የተጫወቱ ወንድማማቾችን እናስታውሳችኋለን፡፡
እንደ ካፍ ኦን ላይን ዘገባ ከኾነ ኢትዮጵያውያኖቹ ወንድማማቾች ኢታሎ ቫሳሎን እና ሉቺያኖ ቫሳሎን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለብሔራዊ ቡድን በጋራ የተጫወቱ የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው እ.ኤ.አ የ1962 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፈው ኢትዮጵያን የዋንጫ ባለቤት ካደረጓት ሥብሥብ ውስጥ ወንድማማቾቹ ኢታሎና ሉቺያኖ ቫሳሎን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሉቺያኖ ቫሳሎን በዚያ ውድድር ላይ የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለማንቸስተር ሲቲ (በጋራ) እና በተናጠል ደግሞ ኮሎ ቱሬ ለአርሰናል እንዲኹም ያያ ቱሬ ለማንቸስተር ሲቲ በተቃራኒነት ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡
ኮሎ ቱሬ እና ያያ ቱሬ ሀገራቸው አይቮሪኮስት በ2006፣ 2008፣ 2010፣ 2012፣ 2013 እና በ2015 (እ.ኤ.አ) በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ የቡድናቸው ወሳኝ ጠጨዋቾች ነበሩ፡፡ በ2015 ከሀገራቸው ጋር ዋንጫን አሳክተዋል፡፡
አንድሬ አየው እና ጆርዳን አየው ምንም እንኳን በአንዱም የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ላይ ዋንጫን ባያሳኩም በስድስት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለሀገራቸው ተጫውተዋል፡፡
የታዋቂው እግር ኳሰኛ አቤዲ ፔሌ ልጆች የኾኑት አንድሬ አየው እና ጆርዳን አየው በ2012፣ 2015፣ 2017፣ 2019፣ 2021 እና 2023 ለጋና ብሔራዊ ቡድን በጋራ ተጫውተዋል፡፡
የካሜሮኖቹ ወንድማማቾች አንድሬ ቢክ እና ፍራንኮይስ ቢክ በ1988፣ 1990 እና 1992 በጋራ ለካሜሮን ብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ሲኾን በ1988 ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳም ሁለቱ ወንድማማቾች በጋራ የድሉ ባለቤቶች አባል ነበሩ፡፡
በ1990 የዓለም ዋንጫ ላይ ወጣት የነበረው ካሜሮናዊ ፍራንኮይስ ቢክ በማራዶናዋ ሀገር አርጀንቲና ላይ ግብ ማሶቆጠሩንም ታሪክ መዝግቦለታል፡፡
ሆሳም ሀሰን እና ኢብራሂም ሀሰን በ1986 እና በ1998 በጋራ ለሀገራቸው ግብጾች በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፈው በሁለቱም ውድድሮች ላይ ዋንጫን አሳክተዋል፡፡
ሆሳም እና ኢብራሂም ሀሰን ወንድማማቾች ኾነው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ በማሳካት ብቸኛ ባለታሪኮች ናቸው፡፡ ሆሳም ሀሰን አኹን ላይ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መኾናቸው ይታወቃል፡፡
አላይን ትራኦሬ እና በርትራንድ ትራኦሬ ለቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን በ2015 እና በ2017 በአፍሪካ ዋንጫ በጋራ ተጫውተዋል፡፡
ሁለቱ የቡርኪናፋሶ ወንድማማቾች በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ከቡርኪናፋሶ ጋር ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቃቸው ለራሳቸውና ለሀገራቸው የነሐስ ሜዳሊያን ማስገኘት ችለዋል፡፡
የማሊዎቹ ሳምቡ ያትባሬ እና ሙስጠፋ ያትባሬ በ2015 እና በ2017 ለሀገራቸው ማሊ በጋራ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ወንድማማቾች ናቸው፡፡
ዛምቢያዊ ወንድማማቾቹ ክሪስቶፈር ካቶንጎ እና ፍሊክስ ካቶንጎ በ2012 እና በ2013 በጋራ ለሀገራቸው በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ዛምቢያ በ2012 የአፍሪካን ዋንጫ ስታነሳ ሁለቱ ወንድማማቾችም አብረው የድሉ ባለቤት ኾነዋል፡፡ በ2023 ሞሪታኒያ አራት ወንድማማቾችን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በማሳተፍ አስገራሚ ታሪክን ጽፋለች፡፡
ኖህ ሞሃመድ፣ ሰኢድ አህመድ ሞሃመድ፣ ላሚኔ ባ እና ሐጂ ባ የተባሉት የኤል ኤቢዲ ልጆች ናቸው ለሞሪታኒያ ብሔራዊ ቡድን በጋራ የተጫወቱት፡፡
የዴሞክራቲክ ኮንጎዎቹ አልበርት ብዋንጋ እና ካዚድ ብዋንጋ በወንድማማች ጥምረት የአፍሪካ ዋንጫን ካሳኩ ወንድማማቾች ውስጥ ስማቸው ይጠቀሳል፡፡
ሁለቱ ወንድማማቾች በ1974 ከሀገራቸው ኮንጎ ጋር የድል ባለቤት ኾነዋል፡፡ የጋናዎቹ አሳሞሃ ጊያን እና ታላቅ ወንድሙ ባፎር ጊያን በ2008፣ የዚምባቡዌዎቹ ፒተር ኒዶቩ እና አዳም ኒዶቩ በ2004፣ የቤኒኖቹ ቶሞጎ ኦማር እና ሲዳት ኦማር በ2000፣ ሞሃመድ ካሎን እና ሙሳ ካሎን ለሴራሊዮን በ1996፣ ሳሚር ሴሊሚ እና አዴል ሴሊሚ ለቱኒዚያ በ1994 በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ወንድማማቾች ናቸው፡፡
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ ሲካሄድ ደግሞ ምን ዓይነት አዝናኝ ታሪኮችን ይዞልን እንደሚመጣ በጉጉት የምንጠብቀው ይኾናል፡፡
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here