በሊጉ የደረጃ ለውጥ የሚያስከትሉ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

0
15
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጉበታል።
ሊቨርፑል በሜዳው ብራይተንን የሚጋብዝበት ጨዋታ ሁነኛ የደረጃ ለውጥን ያስከትላል።
ሊቨርፑል ከ15 ጨዋታዎች በሰባት ጨዋታዎች አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ተለያይቶ እና በስድስት ጨዋታዎች ተሸንፎ 23 ነጥብ በመሰብሰብ ነው 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው።
ቀዮቹ በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የጣልያኑን ኢንተር ሚላንን አንድ ለዜሮ ማሸነፋቸው ለዛሬው ጨዋታ ጥሩ መነቃቃትን ይፈጥርለታል ተብሏል።
ከአሠልጣኝ አርኔ ስሎት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባት በተጠባባቂነት የተያዘው ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ በዛሬው ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መካተቱ ተነግሯል።
ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈም ደረጃውን ከፍ ማድረግ ያስችለዋል።
ብራይተን በበኩሉ ከ15 ጨዋታዎች የተሸነፈው በአራት ጨዋታዎች ነው። 23 ነጥብ በመያዝ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደአውሮፖ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ በ20 ጨዋታ ተገናኝተዋል።
ሊቨርፑል በ12 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነትን ይዟል።
ብራይተን ሊቨርፑልን ያሸነፈው በአራት ጨዋታዎች ሲኾን በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ብራይተን ጨዋታውን ካሸነፈ ይበልጥ ደረጃውን ከፍ ማድረግ ስለሚያስችለው ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ተጠብቋል።
በሌላ የምሽት 12:00 ጨዋታ ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ከኤቨርተን ይጫወታል።
25 ነጥብ በመያዝ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቼልሲ ኤቨርተንን ከሻነፈ አንድ ደረጃ ማሻሻል ያስችለዋል።
24 ነጥብ በመሠብሠብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኤቨርተን ደግሞ ቼልሲ ድል ከነሳ ደረጃውን በሦስት ከፍ ማድረግ ይችላል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በ194 ጨዋታዎች ተገናኝተው ቼልሲ በ77 ጨዋታ አሸንፏል። ኤቨርተን ደግሞ በ60 ጨዋታዎች ድል አድርጓል። በ57 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በቅርብ በተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች ቼልሲ በሁለቱ ሲረታ ኤቨርተን ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በሁለት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የቼልሲው አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ “የቅርብ ጊዜ ችግሮቻቸውን ወደ ኋላ ትተን ለማሸነፍ እንጫወታለን” ብለዋል።
ኤቨርተን ባለፉት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። ይህንን ብቃቱን ለመድገምም ስለሚጫወት ለቼልሲ ከባድ ፈተና እንደሚኾን ይጠበቃል፡፡
የኤቨርተኑ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞይስ “ቼልሲዎች በጣም ጥሩ የተጫዋች ስብስብ አላቸው። እኛም በጥሩ መንፈስ ላይ እንገኛለን። ስለዚህ ለማሸነፍ በቁርጠኝነት እንጫወታለን” ማለታቸውን ለንደን ኢቭንኒግ ስታንዳርድ አስነብቧል።
ከቼልሲ እና ከኤቨርተን አሸናፊው ቡድን ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ ማድረግ ያስችለዋል።
ምሽት 2:30 ሰዓት በርንሌይ ከፉልሃም እንዲሁም አርሰናል ከወልቭስ ምሽት 5:00 ሰዓት ይጫወታሉ።
ሊጉን አርሰናል ሲመራው፣ ማንቸስተር ሲቲ ሁለተኛ አስቶን ቪላ ደግሞ የሦስተኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ።
ዌስት ሃም፣ በርንሌይ እና ዎልቨርሃምፕተን ወራጅ ቀጣና ላይ ተቀምጠዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here