ባሕር ዳር ከተማ በኢትዮጵያ ዋንጫ ከቦዲቲ ከተማ ዛሬ ይጫወታል።

0
13
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦሥተኛ ዙር ዛሬ አራት ጨዋታዎችን በሀዋሳ እና አዲስ አበባ ከተሞች ያስተናግዳል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀን 7፡00 ሰዓት ላይ ባሕር ዳር ከተማ ከቦዲቲ ከተማ ጋር ይጫወታል።
የጣናው ሞገድ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛው ዙር ሸገር ከተማን 2 ለ 0 በማሸነፍ ነው ለሦሥተኛው ዙር ጨዋታ የደረሰው።
ቡድኑ በሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው ጨዋታዎች መረዳት እንደሚቻለው ወጥ አቋም ይዞ መዝለቅ አልቻለም። በመኾኑም እስካሁን ካደረጋቸው ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው 12 ነጥብ ብቻ ነው።
ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይም 11ኛ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ቦዲቲ ከተማ በበኩሉ በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ሀላባ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፎ ነው ለዚህ ጨዋታ የበቃው። የቦዲቲ ከተማ ቡድን በከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ላይ ተደልድሎ ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል።
እስካሁንም አራት ጨዋታዎችን በማከናዎን አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም።
በሁለት ጨዋታዎች ላይ አቻ በመለያየት እና ሁለት ነጥብ ብቻ በመያዝ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ይገኛል።
በዛሬው ጨዋታ በአሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚሠለጥነው ባሕር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኝ እና ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ያሰባሰበ ቡድን በመኾኑ ቦዲቲ ከተማን በቀላሉ ይረታዋል የሚሉ የስፖርት ቤተሰቦች በርካቶች ናቸው።
በሌሎች ጨዋታዎች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ረፋድ 4፡00 ሰዓት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ይጫወታሉ። ቀን 9:30 ሰዓት ደግሞ ኢትዮጵያ መድን ከቢሾፍቱ ከተማ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይኾናሉ።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ቀን 9:30 መቻል ከድሬ ዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።
አሸናፊ ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉ መኾናቸውንም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here