ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፖ ሻምፒዮንስ ሊግ ስድስተኛ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎችን በተለያዩ ከተሞች ያስተናግዳል።
ሪያል ማድሪድ በሜዳው ማንቸስተር ሲቲን የሚገጥምበት ጨዋታ ደግሞ የምሽቱ ትልቅ ጨዋታ ነው።
ሪያል ማድሪድ ከአምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ እና በአንዱ ተሸንፎ በ12 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከአምስት ጨዋታዎች ያሸነፈው በሦሥቱ ብቻ ነው። በአንድ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ በ10 ነጥብ 12ኛ ላይም ተቀምጧል።
ኤአይስኮር እንዳስነበበው ሁለቱ ቡድኖች ከ2012 ወዲህ በ16 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል።
ሪያል ማድሪድ በስድስት ጨዋታዎች በማሸነፍ ቀዳሚ ነው።
በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ማንቸስተር ሲቲ በአምስት ጨዋታዎች ነው ያሸነፈው።
ከ16 ጨዋታዎች ስምንቱ በሳንቲያጎ ቤርናቡ የተከናዎኑ ሲኾኑ በዚህ ሜዳ ሪያል ማድሪድ በአምስት ጨዋታዎች ድል በመንሳት የበላይ ነው።
ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው ያሸነፈው። ዛሬስ?
ሪያል ማድሪድ በላሊጋው በሁለተኛነት ሲገኝ ማንቸስተር ሲቲም በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ነው። ታዲያ ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንጻር ዛሬ የሚገናኙበት ጨዋታም ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡
የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ዣቢ አሎንሶ የቀድሞ አሠልጣኙን ፔፕ ጋርዲዮላ መግጠሙ ደግሞ ሌላው የጨዋታው ጌጥ ይኾናል ተብሎ ተጠብቋል።
በሪያል ማድሪድ በኩል ኬሊያን ምባፔ በገጠመው ጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ኾኗል።
በማንቸስተር ሲቲ በኩል ሮድሪ እና ማቲዮ ኮቫችቺ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ጨዋታው በግዙፉ በሳንቲያጎ ቤርናቡ ምሽት 5 ሰዓት ይደረጋል።
የስፔኑ አትሌቲክ ክለብ የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንት ጄርሜንን ከ53 ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘው ስታዲዮ ደ ሳን ማሜስ የሚጋብዝበት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
ፓሪስ ሴንት ጄርሜን በሊጉ አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ በአራቱ አሸንፏል። በአንድ ጨዋታ ተሸንፏል። 11 ንጹህ የግብ ክፍያ በመያዝ እና 12 ነጥብ በመሰብሰብ በአራተኛነት ተቀምጧል።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደግሞ ደረጃውን ወደ ሁለተኛነት ከፍ ማድረግ ስለሚያስችለው ጨዋታው ወሳኝ ነው።
አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ተጫዋቾች በአካላም በቴክኒክም ብቁና ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ብለዋል። ዛሬ አሸንፈን አንደኛ ለመኾን ነው ፍላጎታችን ሲሉ ተደምጠዋል።
ተጋጣሚው የአትሌቲክ ክለብ ከአምስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ ተለያይቶ እና በሦሥቱ ተሸንፎ አራት ነጥብ በመያዝ 28ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የቤልጅየሙ ክለብ ብሩዥ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
አርሰናል እስካሁን ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በማሸነፍ 13 ንጹህ የግብ ክፍያ በመያዝ እና 15 ነጥብ በመሰብሰብ ሻምፒዮንስ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
መድፈኞቹ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ መሪነታቸውን ለማጠናከር ይጫወታሉ።
ተጋጣሚው ክለብ ብሩዥ ደግሞ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በሦሥት ጨዋታዎች ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ 27ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኑ በሻምፒዮንስ ሊጉ ደረጃው ቢያሽቆለቁልም በቤልጅየም ፕሮ ሊግ ግን ጠንካራ ተፎካካሪ በመኾን ሦሥተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ20 ሺህ በላይ ተመልካች በሚያስተናግደው ዣን ብሬያዴል ስታዲየም ምሽት 5 ሰዓት ይገናኛሉ።
ምሽት 5 ሰዓት ላይ ጁቬንቱስ ከ ፓፎስ፣ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ከ ቡዶ ጊልሜት፣ ባየር ሊቨርኩሰን ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ቪላሪያ ከኮፕንሃገን እና ቤኔፊካ ከ ናፖሊ ሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ቪላሪያ ከ ኮፕንሃገን እና ካራባግ ከአያክስ ምሽት 2:45 ይጫወታሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



