ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ነው። በኳስ ቁጥጥር፣ እንደ አቦሻማኔ በሚሸመጥጥ ፍጥነቱ እና በጎል የማስቆጠር ችሎታው ይታወቃል፡፡ ለተጋጣሚ የማይመች፣ በአንድ ለአንድ ግንኙነት አደገኛ እና የተዋጣለት እንቅስቃሴው እሱን መቋቋም አዳጋች ያደርጉታል።
ከፈረንሳይና አልጀሪያዊት ቅይጥ እናቱ ፋይዛ ላማሪ እና ከካሜሮናዊ አባቱ ከዊልፍሬድ ምባፔ ነው የተወለደው፡፡እናቱ የቀድሞ የእጅ ኳስ ተጫዋች አባቱ ደግሞ የእግር ኳስ አሠልጣኝ እንደነበሩ እና ለልጃቸው የዛሬ የእግር ኳስ ማንነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ራሱ ሠስክሯል።
በአሁኑ ጊዜ ለሪያል ማድሪድ እና ለፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን በአጥቂነት ይጫወታል፤ ኪልያን ምባፔ፡፡ የእግር ኳስ ሕይወቱን በፈረንሳይ ሞናኮ ክለብ ነው የጀመረው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2017 ድረስ በሞናኮ እና ከ2017 እስከ 2024 በፒኤስጂ የተጫዎተ ሲኾን ከ2024 ጀምሮ ደግሞ በሪያል ማድሪድ ይገኛል፡፡ ለብሔራዊ ቡድኑም ቋሚ ተሰላፊ እና አምበልም ነው አሁን።
1 ነጥብ 78 ሜትር ርዝመት ያለው ፈረንሳዊው አጥቂ ኪልያን ምባፔ በሀገሩ ታሪክ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጎል ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ነው፡፡ ከፒኤስጂ በነጻ ዝውውር ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ምባፔ ሳምንታዊ ደመወዙ 629 ሺህ 355 የአሜሪካን ዶላር ሲኾን የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ መኾኑን ጎል ዶት ኮም አስነብቧል፡፡ በነጮቹ ቤት የአምስት ዓመት ኮንትራት መፈረሙም ይታወሳል፡፡
ምባፔ አሁን በተለያዩ ምክኒያቶች ለሚታመሰው ሪያልማድሪድ በግሉ ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ነው። የላሊጋውን የ2025/26 የጎል አስቆጣሪነት ደረጃ በ16 ጎሎች እየመራ ነው። 16 ሳምንታትን በተጓዘው የላሊጋ ሂደት ምባፔ በአማካኝ በጨዋታ አንድ ግብ አስቆጥሯል። ይሄም ተጫዋቹ ያለበትን ድንቅ አቋም የሚያሳይ ነው።
በ26 ዓመቱ 400 ጎሎች በመድረስ ከፔሌ በመቀጠል ሁለተኛው ተጫዋች መሆኑን ቢን ስፖርት አስነብቧል። በስኬት ማማ ላይ የሚገኘው ፈረንሳዊ አጥቂ ኪልያን ምባፔ በሁለት የዓለም ዋንጫ በ14 ጨዋታዎች ተሰልፎ 12 ጎሎችን በማስቆጠር እና አንድ ዋንጫ በማሸነፍም የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍነቱን አስመስክሯል፡፡
በግልምሆነ በቡድን የዓለም ዋንጫን ጨምሮ ትልልቅ ክብሮችን ገና በወጣትነቱ ማሳካት የቻለ ካለፈው ይልቅ መጭው የእግር ኳስ ህይወቱ በጉጉት የሚጠበቀው ምባፔ በሪያል ማድሪድ ቤት መንገዱ ሠምሮለታል።
ማድሪድን በተቀላቀለበት ያለፈው የውድድር ዓመት በ31 ግቦች የላሊጋው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበር። ዘንድሮም ከወዲሁ 16 ግቦችን በማስቆጠር የስኬት መንገድ ላይ ነው።
በዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን



