የዋንጫ ተፎካካሪነቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርገው የምሽቱ ጨዋታ፦

0
84
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ)‎ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ በሚካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ደግሞ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ኾኖ ለመውጣት ጥረት እያደረገ ያለው ማንቸስተር ሲቲ ከፉልሀም ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ማንቸስተር ሲቲ ከሊጉ መሪ አርሰናል በአምስት ነጥብ ርቆ በ25 ነጥብ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል። የጋርዲዮላው ቡድን ለጊዜውም ቢኾን ይህን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያጠባል።
በዚህም ምክንያት ሲቲ ከፉልሀም ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ወሳኝ ነው።
በሊጉ በኒውካስትል ዩናይትድ እና በቻምፒዮንስ ሊጉ በባየር ሊቨርኩሰን ተከታታይ ሽንፈትን የተጎነጨው ማንቸስተር ሲቲ በ13ኛ ሳምንቱ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሊድስ ዩናይትድን 3ለ2 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት መንፈስ መመለስ ችሏል።
ቡድኑ ያገኘው ውጤትም በሊጉ ወደ ሁለተኛ ደረጃ እንዲመጣ እና ከመሪው ቡድን ጋርም ያለውን ልዩነት እንዲያጠብ ረድቶታል።
ተጋጣሚው ፉልሀምም ቢኾን ምንም እንኳን በሊጉ ባለፉት ጨዋታዎች ደረጃው ወርዶ በ17 ነጥብ 15 ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ጥሩ ተፎካካሪ የሚባል ክለብም ነው።
ፉልሀም በሊጉ በተከታታይ እንደ ሰንደርላንድ እና ቶትንሀም ሆትስፐር ያሉ ቡድኖችን በማሸነፍ የተሻለ አቋም ላይ ያለ ቡድን በመኾኑ ለሲቲ በቀላሉ እንደማይሸነፍ ማሳያ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች እስካሁን 58 ጊዜ ሲገናኙ ይህኛው ለ59ኛ ጊዜ ይኾናል። በዚህ ጨዋታም 37 ጊዜ ሲቲ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ደግሞ ፉልሀም ማሸነፍ ችሏል። ቀሪ ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተለያዩባቸው ናቸው።
በቅርቡ ካደረጓቸው የሊጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲቲ ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው። ጥያቄው ወጥነት የሚጎድለው ሲቲ የበላይነቱን አስጠብቆ በሊጉም ተፎካካሪነቱን ያስቀጥላል የሚለው ነው? ጨዋታውም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ምሽት 4፡30 ይካሄዳል።
ሌሎች የሊጉ ሁለት ጨዋታዎችም ሲካሄዱ በርንማውዝ ኤቨርተንን የሚጋብዝበት ጨዋታ 4፡30 ይደረጋል።
ኒውካስትል ቶትነሀም ሆትስፐርን የሚጋብዝበት ጨዋታ ደግሞ ምሽት 5፡15 ላይ እንደሚካሄድ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here