ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጣልያን ሴሪኤ 13ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 4:45 ሮማ ናፖሊን የሚጋብዝበት ጨዋታ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ነው።
ሴሪኤውን ኤሲ ሚላን 13 ጨዋታዎችን በማድረግ 28 ነጥብ እና 10 ንጹህ የግብ ክፍያ በመሠብሠብ እየመራው ይገኛል።
ሮማ ደግሞ ከ12 ጨዋታዎች 27 ነጥብ እና ዘጠኝ ንጹህ የግብ ክፍያ በመያዝ በሁለተኛነት ተቀምጧል።
ናፖሊ በበኩሉ ከ12 ጨዋታዎች 25 ነጥብ ሰብስቧል። ስምንት ንጹህ የግብ ክፍያም አለው። ደረጃው ደግሞ ሦስተኛ ነው።
በሴሪኤው በሁለተኛነት እና በሦስተኛነት የሚገኙት ሮማ እና ናፖሊ ምሽት 4:45 የሚያደርጉት ጨዋታ አሸናፊው ቡድን ደረጃውን ከፍ የሚያደርግበት በመኾኑ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።
ሁለቱ ቡድኖች 70ሺህ ተመልካች በሚይዘው በስታዲዮ ኦሊምፒኮ ( የኦሊምፒክ ስታዲየም) ባደረጓቸው የቅርብ 20 ጨዋታዎችን ባለሜዳው ሮማ ዘጠኝ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የበላይነቱን አስመስክሯል።
ናፖሊ በስድስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በጨዋታው ሮማ ካሸነፈ ነጥቡን 30 በማድረስ የሴሪኤው መሪ ያደርገዋል።
በአንጻሩ ናፖሊ ድል የሚያደርግ ከኾነ ነጥቡ ከኤሲ ሚላን ጋር የሚስተካከል ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
በሙሉጌታ ሙጨ



