በለንደን ደርቢ ማን ይነግሳል?

0
71
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በለንደን ደርቢ ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ አርሰናልን የሚጋብዝበት ጨዋታ በጉጉት ተጠባቂ ኾኗል፡፡
ቼልሲ በፕሪምየር ሊጉ እስካሁን 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በሰባቱ አሸንፏል፡፡ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል፡፡ በሦስቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡ 12 ንጹሕ የግብ ክፍያ በመያዝ እና 23 ነጥብ በመሰብሰብም ሦስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ተጋጣሚው አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ሲለያይ የተሸነፈው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በዘጠኝ ጨዋታዎች አሸንፎ እና 18 ንጹሕ የግብ ክፍያ በመያዝ እና 29 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪምየር ሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
አርሰናል ዛሬ ምሽት 1:30 በስታምፎርድ ብሪጅ ከቼልሲ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ መሪነቱን ይበልጥ በማጠናከር ከ22 ዓመት በኋላ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት የሚኖረውን ተስፋ ከሌሎች ቡድኖች የተሻለ ያደርጋል፡፡
ኤአይኤስ ስኮር ዶት ኮም እንዳስነበበው ሁለቱ ቡድኖች ከ1995 ጀምሮ በ78 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ አርሰናል በ29 በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ ቼልሲ ደግሞ ማሸነፍ የቻለው በ26ቱን ጨዋታዎች ነው፡፡
በተጨማሪ ሁለቱ በታሪካቸው ያደረጉትን 189 ጊዜ ተገናኝተዋል። አርሰናል በ74 ጨዋታ ሲያሸንፍ ቸልሲ ያሸነፈው በ60 ጨዋታዎች ነው፡፡ በ55 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል። ሁለቱ ቡድኖች ከተጠቀሰው አሃዝ ውስጥ 96 ጨዋታዎችን ያደረጉት በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ነው፡፡
በዚህም አርሰናል በ46 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነቱን ወስዷል፡፡ ቸልሲ አርሰናልን ያሸነፈው በ26 ጨዋታዎች ብቻ ነው ይላል መረጃው፡፡ በ24 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ከ189 ጨዋታዎች መካከል ደግሞ 176ቱ ጨዋታዎች በፕሪሚየር ሊጉ የተደረጉ ሲኾኑ አርሰናል በ70 ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ቸልሲ 54ቱን አሸንፏል፡፡ 52ቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ተጠናቅቀዋል፡፡
የቸልሲው አለቃ ኤንዞ ማሬስካ ”ጨዋታውን በውድድር ዓመቱ ከሚደረጉ ጠንካራ ጨዋታዎች አንዱ ነው፤ የአርሰናል ስብስብ ጥሩ ነው፡፡ እኛም እንዲሁም ጠንካራ ቡድን ሰርተናል፡፡ እኛ 12 ተጨዋቾችን ስናሰልፍ እነርሱ ማሰለፍ የሚችሉት 11 ተጫዋቾችን ብቻ ነው፡፡ የሜዳ ዕድላችንን በመጠቀም ተጭነን በመጫወት እናሸንፋልን ብለዋል፡፡
አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ለስካይ ስፖርትስ ጨምረው እንደተናገሩት ኮል ፓልመር ከጉዳቱ ተመልሷል፡፡
የአርሰናል አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ በበኩላቸው “ጨዋታው ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት ነው፡፡ እግር ኳስ ወዳዱ የዓለም ሕዝብም በጉጉት የሚጠብቀው የለንደን ደርቢ ነው ብለዋል። እነርሱ (ቸልሲ) በጣም ጥሩ አቋም ላይ ናቸው ፡፡ሊፈትኑን ቢችሉም ለጨዋታው ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ኾነን በመቅረባችን እናሸንፋለን” ነው ያሉት፡፡
ጉዳት ላይ የነበሩት ካይ ሀቨርዝ እና ቪክቶር ዮኬሬስም ሊሰለፉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ጨዋታውን የ47 ዓመቱ ዳኛ አንቶኒ ቴለር በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here