ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች 15 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ዛሬ ከወላይታ ዲቻ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ አሸንፎ ወደ መሪነት ለመመለስ ጨዋታውን ያደርጋል።
ፋሲል ከነማ በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን 1ለ0 አሸንፎ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የመጣ ሲኾን የዛሬውን ሦስት ነጥብ ማሳካት ከቻለ ነጥቡን 18 በማድረስ 16 ነጥብ ይዞ ሊጉን እየመራ ካለው ሲዳማ ቡና ደረጃውን ይረከባል።
በሌላ በኩል ተጋጣሚው ወላይታ ዲቻ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2ለ1 በማሸነፍ በሊጉ በ5 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ክለብ ነው።
ክለቡ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ፣ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዶ ወደ መጀመሪያ ድሉ የመጣ ክለብ ነው።
ክለቡ በሰባተኛ ሳምንት ያገኘው የማሸነፍ ሥነ ልቦና ዛሬ ለፋሲል ከነማ ጋር ፈታኝ ሊኾንበት እንደሚችል አመላካች ኾኗል። ጨዋታውም ቀን 7፡00 ላይ ይደረጋል።
ዛሬ ሌላው በሊጉ ተጠባቂው ጨዋታ የባሕር ዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ነው። ባሕር ዳር ከተማ በሊጉ በሰባት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ ይዞ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ክለብ ነው።
ባሕር ዳር ከተማ በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ በአዳማ ከተማ ከደረሰበት የ1ለ0 ሽንፈት በኋላ ዛሬ ለመውጣት ነው ጨዋታውን የሚያደርገው።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ እስካሁን በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ማግኘት የቻለው ነጥብ ስምንት ሲኾን ይህም ደረጃውን ወደ 13 ዝቅ እንዲል አድርጎታል።
ኢትዮጵያ መድን በሰባተኛ ሳምንት ጨዋታው ከነገሌ አርሲ ጋር ተገናኝቶ 1ለ0 ሽንፈትን አስተናግዷል።
ቡድኑ ታዲያ ዛሬ በሚያደርገው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነው ጨዋታውን የሚያደርገው። ጨዋታውም 9፡00 ላይ መካሄድ ይጀምራል።
በሊጉ ዛሬ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ጨዋታዎችም ሲካሄዱ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማ 12፡00 ላይ ጨዋታቸው ሲጀምር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቀለ 70 እንደርታ 10፡00 ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



