ማንቸስተር ሲቲ ደረጃውን ለማሻሻል፤ ሊድስ ዩናይትድ ደግሞ ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

0
47
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ስታዲየም ከሊድስ ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ማንቸስተር ሲቲዎች 12 ጨዋታዎችን አድርገው ሰባቱን በማሸነፍ፣ በአንዱ አቻ በመለያት እና በአራት ጨዋታዎች በመሸነፍ በ22 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ስፖርትስ ሞል እንዳስነበበው ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው 110 ጨዋታዎች ላይ ተገናኝተዋል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ በ49 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ በ18 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሊድስ ዩናይትድ ደግሞ በ43 ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ጋርዲዮላ በተጨዋቾቹ ብቃት እምነት እንደያዙ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በኳስ ላይ በጣም ጠንቃቃ በመኾን ስህተት ላለመሥራት ብሎም ለማሸነፍ እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል፡፡
ቡድኑ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ አርሰናል ያለውን የሰባት ነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ለማድረግ ማሸነፍ ግድ ነው፡፡ በጨዋታው ማንቸስተር ሲቲ 4-1-4-1 አሰላለፍን ይከተላል ተብሏል፡፡ የፊት መስመሩንም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኧርሊንግ ሃላንድ እንደሚመራው ተገልጿል፡፡
በጨዋታው ማቲዩ ኮቫቺች በጉዳት የማይሰለፍ ይኾናል። ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታውን ካሸነፈም ሁለተኛ ደረጃን የሚይዝ ይኾናል፡፡
ሊድስ ዩናይትድ በበኩሉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በሦስቱ አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ወጥቶ እና በሰባት ጨዋታዎች ተሸንፎ እንዲሁም በ11 የግብ ዕዳ 11 ነጥብ በመሰብሰብ በወራጅ ቀጣናው ላይ ይገኛል፡፡ በመኾኑም በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከቀዩ መስመር እንዲርቅ ያደርገዋል፡፡
በአሠልጣኝ ዳንኤል ፋርክ ቡድኑ በገባበት የውጤት ቀውስ የተበሳጩ ደጋፊዎች አሠልጣኙ እንዲሰናበት ድምጽ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ ይህን ተከትሎም አሠልጣኙ “እኔ በራሴ ላይ አላተኩርም፤ አሁን የማስበው ማንቸስተር ሲቲን እንዴት እንደምናሸንፍ ነው” ብለዋል። ጫጫታው በእኔ ላይ እንጂ በተጫዋቾቹ ላይ ባለመኾኑም ወድጄዋለሁ ነው ያሉት።
ሊድስ በዛሬው ጨዋታ 4-5-1 አሰላለፍን ይተገብራል። የፊት መስመሩንም ሉካስ ንሜቻ ይቆጣጠረዋል ነው የተባለው፡፡ ጨዋታውን ማንቸስተር ሲቲ በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸንፋል የሚሉ በርካቶች መኾናቸውን ዴይሊ ሜይል ስፖርት አስነብቧል፡፡
ሊጉን አርሰናል ሲመራው ቼልሲ ይከተላል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ በሦስተኛነት ተቀምጧል፡፡ ሊድስ ዩናይትድ፣ በርንሌይ እና ዎልቨርሃምፕተን ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here