ደሴ ከተማ ዛሬ ከመሪዎቹ ተርታ የሚያደርሰውን ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል።

0
47

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች የአምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬም በጅማ እና ሃዋሳ ከተሞች ቀጥለው ይውላሉ፡፡

ቀን 9:30 ሰዓት የአማራ ክልል ተወካዩ ደሴ ከተማ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በጅማ ስታዲየም ይጫወታል፡፡

ደሴ ከተማ እስካሁን አራት ጨዋታዎችን አድርጎ በአንዱ አሸንፎ እና በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቶ አምስት ነጥብ እና አንድ ንጹሕ የግብ ክፍያ በመያዝ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን ስምንት በማድረስ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ከመሪዎቹ ተርታ ይሰለፋል፡፡

ተጋጣሚው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ፣ በአንዱ አቻ ተለያይቶ እና በአንዱ ተረትቶ አራት ነጥብ በመያዝ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድን የቴክኒክ ዳይሬክተር አብርሐም ተስፋ ለአሚኮ እንደገለጹት ተጨዋቾች በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ ለማሸነፍም በቴክኒክ፣ በታክቲክ እና በሥነ ልቦና ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡

የሚጫዎቱት አሸንፈው ሦስት ነጥብ በማስመዝገብ ከመሪዎች ጋር እኩል ለመኾን እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

በጅማ እና አካባቢው የሚገኙ የቡድኑ ደጋፊዎች እስካሁንም በድጋፍ አልተለዩንም ያሉት ዳይሬክተሩ ዛሬም ስፖርት ቤተሰቡ የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ የምድብ ”ለ” ጨዋታ ቀን 7:00 ሰዓት ላይ ቢሾፍቱ ከተማ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል፡፡
በሐዋሳ ሰው ሠራሽ ሳር በተነጠፈለት ሜዳ ደግሞ ቀን 7:00 ሰዓት ቤንች ማጂ ቡና ከንብ እንዲሁም 9:30 ሰዓት ሻሸመኔ ከተማ ከነቀምቴ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ትናንት ሱሉልታ ክፍለ ከተማን የገጠመው ደብረ ብርሃን ከተማ 1 ለ 0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here