ባሕር ዳር፡ ኅዳር 16/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር፣ የብዙ አትሌቶች መፍለቂያ እና የኢትዮጵያ ድምቀት የኾነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25 ዓመታትን በስኬት ተጉዟል።
በ10ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መዝግቦ በ1994 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ55 ሺህ በላይ ሰዎችን ተሳታፊ አድርጓል። ሺህዎች የሮጡበት ሚሊዮኖች የወደዱት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፎ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ያገኘ የሀገር መለያ ኾኗል።
በየዓመቱ ኅዳር ወር ዕድሜ፣ ጾታ እና ሌሎች ጉዳዮች ሳይገድቡት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ ይታደሙበታል። ተሳታፊዎች አንድነትን ፈጥረው እና በሀገራቸው ሰንደቅ አላማ ቀለም በተዋበ አለባበስ ደምቀው በፍቅር ይዘምሩበታል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫ በላይ ነው። ፖለቲካ እና ዘር ተመዞ አቲካራ የማይገጠምበት፤ የእርስ በርስ መነቋቆር የማይገኝበት፤ የጸብ ሽታ ውልብ የማይለይበት፤ ሁሉም የሚፈነጥዝበት ቀለም ነው። ደስታ እና ፌሽታ፣ ሙዚቃ እና ጭፈራ በሳቅ ታጅቦ በየፈርጁ የሀገር ፍቅር ያለ ከልካይ ይነግስበታል።
የሀገር እና የወገን ፍቅርን በልቡ ያተመው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከኢቢሳ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ይደርሳል ብሎ አስቦ እንደማያውቅ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ እንዲጀመር ምክንያት የኾነው የሃሳብ ጥንስስም በአውሮፓውያኑ ሚሊንየም ከተደረገው የሲዲኒ ኦሎምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር በኋላ ዳግም በእንግሊዝ ይደረግ በነበረው ታላቅ ሩጫ ውድድር ላይ እንዲሳተፍ የተጠየቀባት አጋጣሚ እንደኾነም አስታውሷል።
በወቅቱም “እንደ እናንተ አይነት ውድድር በኢትዮጵያ እንድናደርግ አግዙን” ብሎ አዘጋጆቹን ጠይቆ ተቀባይነት እና ድጋፍ በማግኘት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሯጮች ተጀምሮ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ መድረሱን ነው የተናገረው።
ኢትዮጵያውያንን በአብሮነት አድምቆ ለሀገሩ ክብር የፈጠረው እና በዓለም መድረክ የበርካታ ሩጫ ውድድሮች ሪከርድ ባለቤት የኾነው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ራሱ ባስጀመረው ሩጫ ላይ ተሳታፊ ኾኖ እስከ 25 ዓመት ዘልቋል። የመጀመሪያው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አሸናፊ እንደነበርም አስታውሷል።
በ25 ዓመት ውስጥ በርካታ አትሌቶች ተሳትፈዋል፤ የተሳተፉትም ወደ ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮች ሲሄዱ ውጤታማ ኾነው አጠናቀዋል፤ ፋይዳው ጉልህ እንደኾነ ነው የገለጸው። ብዙዎች ታላቁ ሩጫ ላይ እስኪወዳደሩ ያላቸውን አቅም አናውቀውም፤ ለማወቅ ዕድል ሰጥቷል ብሏል።
ታላቁ ሩጫ የበጎ አድራጎት እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ከመደገፍ ጋር የተሳሰረም ነው። በየዓመቱም የተለያዩ ለውጦችን ይዞ እንደሚመጣም ነው ያነሳው። ወደፊት ፈጣሪ ጊዜ ከሰጠን ብዙ ነገር የምናይበት ነውም ብሏል ሃይሌ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድባቡ ለየት ያለ ነው። በኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ እና ፍላጎት የተመሠረተ ነው። ይህ ደግሞ እያደገ ለመምጣቱ ምክንያት ኾኖታል፤ አብዛኛው ሰው ከሩጫ ውድድርነት ባለፈ መዝናኛ፣ መሰባሰቢያ እና ደስታ መፍጠሪያ አድርጎታል ይላል የሩጫው ንጉስ።
ከመጀመሪያው የውድድር ዓመት ጀምሮ ሁሉንም ዓመቶች አብረው ከተጓዙ እና ከዘለቁ ሰዎች መካከል ታዲወስ ሁሴን አንዱ ናቸው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሁሉንም በጋራ እና በአንድነት አስተሳስሮ ማገናኘቱ በራሱ ትልቅ ነገር መኾኑን ተናግሯል። የሰላም ተምሳሌት እና ሀገርን የሚያስተዋውቅ ነው ብሏል። ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች ብዙ እንግዶች ለውድድሩ መጠው ሲታደሙ መመልከቱንም ገልጿል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በርካታ አትሌቶች በዓለም አደባባይ እንዲደምቁ፤ ድልን እንዲጎናጸፋ እና የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው እንዲሰቅሉ ምክንያት ኾኗል ይላሉ። ጅምራቸውን በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ አሳምረው በዓለም አቀፍ መድረክ የደመቁ አትሌቶች ብዙ ናቸው ነው ያሉት።
ሰለሞን ባረጋ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይዎት፣ በሪሁን አረጋዊ ከወንዶች እንዲሁም ውዴ አያሌው፣ ያለም ዘርፍ የኋላው እና ዘይነባ ይመር ደግሞ ከሴት አትሌቶች የታላቁ ሩጫ ፍሬዎች ናቸው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለተተኪ አትሌቶች ውለታው ብዙ ነውም ብለዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቃል ይገባበታል፤ በዓመቱ ለመሳተፍ ከወዲሁ መልካም ምኞት ይገለጽበታል፤ ለአንዳንዶችም የውኃ አጣጫቸውን ማግኛ መንገድ ሆኗል። ወዳጅ እና ዘመድ መመሥረቻ እንደኾነም መሥራቹ ሃይሌ አንስቷል።
ለሀገሬው ብቻ ሳይኾን ለሌላውም የዓለም ማኅበረሰብ መገናኛ ኾኖ እያገለገለም ነው። ማንም ሳይጠይቃቸው ለተሳታፊዎች ውኃ የሚያቀብሉ እና የሚያበረታቱ፤ ለደከመው ማረፊያ የሚኾኑ የበጎ ልብ ባለቤት ኢትዮጵያውያን የሚስተዋሉበትም ነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ። ተወዳጅ እና ተናፋቂ እየኾነ የመጣም ነው። ሁለንተናዊ አበርክቶው ጉልህ ነው።
በፈረንጆቹ 2019 በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በዓለም ቀዳሚ ኾኖ መመረጥ የቻለም ነው። በቅርቡ 25ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በሚካሄድበት የዋዜማ ሳምንት የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዘርፉ የዓለም ቅርስ ነው ብሎ እውቅናን ሰጥቶታል።
ይህ የዓለም አትሌቲክስ ቅርስ ከስታዲየም ውጭ ለሚከናወኑ የአትሌቲክስ ዘርፎች በዓለም አቀፍ ታሪክ እና እድገት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ የሚሰጥ ክብር ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



