የአርሰናል የመሰለው ዓመት…

0
62
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርሰናል በእንግሊዝ ትልቅ ከሚባሉ ክለቦች አንዱ ነው። ከእንግሊዝ እና አውሮፓ አልፈው በዓለም አቀፍ እግር ኳስ አፍቃሪያን ተወዳጅ ከሚባሉ ክለቦች መካከልም የአርሰናል ስም ይገኛል።
ታዲያ ክለቡ የስሙን ያህል በተለይ በአውሮፓ መድረክ ውጤት አለማግኘቱ ጥያቄ በየጊዜው ያስነሳበታል። በተጨማሪም ምንም እንኳ ፕሪምየር ሊጉን 13 ጊዜ የማሸነፍ ታሪክ ቢኖረውም ዋንጫውን ካነሳ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
ክለቡ በተለይም በቅርብ ዓመታት በሚኬል አርቴታ ሥር የተሻለ የዋንጫ ተፎካካሪ መኾን ቢችል ወደ ሊጉ የመጠናቀቂያ የሚያሳየው መደነጋገር የማንቸስተር ሲቲና ሊቨርፑል አሯሯጭ አስመስሎታል።
ነገር ግን የዘንድሮው ዓመት የአርሰናል ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ ክለቡ አርሰናል ከራሱ ጥንካሬ በላይ የዋንጫ ተቀናቃኞቹ ደክመው መገኘታቸው ነው። የአምናው የዋንጫ ባለቤት ሊቨርፑል ዘንድሮም በጥንካሬው ቀጥሎ የዋንጫው ባለቤት ይኾናል ሲባል የቁልቁለት ጉዞ ላይ ተገኝቷል።
የአርኒ ስሎቱ ቡድን ገና በ12 የሊጉ ጨዋታ በስድስት ተሸንፏል። የሰበሰበው ነጥብ 18 ሲኾን ከመሪው አርሰናል በ11 ነጥብ ያነሰ ነው።
ሌላኛው የዋንጫ ተፎካካሪ ማንቸስተር ሲቲ ድንገት ባለፈው ዓመት ከመታው መፍረክረክ ዘንድሮም በልኩ ያገገመ አይመስልም። ቡድኑ በ12 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ሰባት አሸንፎ፣ አራት ጊዜ ተሸንፎ እና በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። የሰበሰበው 22 ነጥብም ከአርሰናል በሰባት ያነሰ ነው።
የእነዚህ ሁለት ቡድኖች ደክሞ መገኘት ዘጠኝ አሸንፎ፣ ሁለት ጊዜ ነጥብ ለተጋራው እና አንድ ጊዜ ብቻ ለተሸነፈው አርሰናል ሊጉን በሰፊ የነጥብ ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል።
የአርቴታው ቡድን ከዚህ በፊት ይታማበት የነበረው የቡድን ጥልቅ ዘንድሮ አይነሳም። ለዚህ ማሳያው የቡድኑ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ በጉዳት እየተጫወተ ባይኾንም አዲስ ፈራሚው ኤዜ ለጊዜው ተጫዋቹን አስረስቷል።
በሳሊባ እና ጋብሬል ብቻ የተንጠለጠለ የነበረው የመከላከል ክፍሉም አዳዲስ ፈራሚዎች እድሉን ሲያገኙ ባሳዩት ጥሩ አቋም የአርሰናል ጭንቀት ተቃሏል።
በእነዚህና ተጨማሪ ምክንያቶች ዓመቱ የአርሰናል መስሏል። እንደ ብዙዎች ግምት የአርቴታው ቡድን ዘንድሮ ዋንጫውን የማያገኝ ከኾነ ለክለቡ እንደ እርግማንም ይቆጠራል።
የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ጅሚ ካራጋር አርሰናልን ዋንጫ ለማንሳት የሚቀናቀነው ብቸኛው ተጫዋች ራሱ አርሰናል ብቻ ነው ብሏል ለስካይ ስፖርት። ዋንጫውን ለማንሳት ሁሉ ነገር በእጃቸው ላይ መኾኑን ለመግለጽ ነው ካራገር ይሄን ሀሳብ የገለጸው።
ነገር ግን የውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ አርሰናል በምን ሁኔታ ላይ ሊገኝ ይችላል የሚለው አሁንም የእግር ኳስ አፍቃሪያን ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ቡድኑ ወጣ ሲባል የመውረድ፣ ዋንጫ አነሳ ሲባል ሁለተኛ ኾኖ የጨረሰባቸው የቅርብ አጋጣሚዎች በብዙዎች ህሊና ያቃጭላሉና።
ወራት የሚመልሱት ጥያቄ ለጊዜው የአርሰናል የመሰለው ዓመት በመጨረሻስ?
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here