ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓመታት በፊት እርሱ እና ቤተሰቦቹ ምሳ በልተው እራት አይደግሙም ነበር። ቀጫጫ እና ለግላጋው ታዳጊ ጎዳናዎችን እያጸዳ፣ ትራፊ ቁራሽ የሚመጸውተው የሰው እጅ ይመለከት ነበር። ለትራፊ ምግብ ሲል በየሆቴሎች በር ይቆምም ነበር። የሚሰጥ ሲገኝ እየተመገበ፣ ትራፊ በጠፋ ጊዜ ጾሙን እየተመለሰ ሕይወትን ይገፋ ነበር።
በዚያ ዘመን ከመንደሩ ልጆች ተለይቶ በዓለም ገናና ስም ያለው ሰው ይኾናል ብሎ የገመተ አልነበረም። እርሱ ግን አንድ ቀን ታላቅ ሰው እንደሚኾን ለውስጡ ይነግረው ነበር።
ከመንደሩ ታዳጊዎች ጋር እግር ኳስን ማንከባለል የጀመረው የዚያኔው ብላቴና የአስደናቂ ተሰጥኦ ባለቤት መኾኑን ለማሳየት ጊዜ አልወሰደበትም። ኳስን እንደ አሻው የሚያንከባልለው፣ ከፍጥነቱ ሳይደናቀፍ ኳስ እየነዳ ተጋጣሚዎችን የሚያልፈው ብላቴና ለእግር ኳስ መፈጠሩን አስቀድሞ ተረድቷል።
እግር ኳስ የእርሱንም ኾነ የቤተሰቦቹን ሕይወት መቀየር እንደሚችል የተረዳው ብላቴናው ለእግር ኳስ ጠንክሮ ሠራ። እግር ኳስም የልፋቱን ዋጋ እጥፍ ድርብ አድርጋ ሰጠችው።
ያ “የማደራው” ልዑል ክርስቲያኖ ሮናልዶ በጥረቱ ረሃብን ታሪክ አድርጎ፣ የማይቻሉ የማይመስሉ ታሪኮችን ሠርቶ ስሙን በደማቅ ቀለም ላይ አጽፏል። ዛሬ ላይ ቢሊየነር ነው።
በፖርቹጋል ማዴራ ከደሃ ቤተሰብ የተገኘው ብላቴና በጠንካራ ሥራው የዓለምን እግር ኳስ ተቆጣጥሯል። ዝናው በዓለሙ ሁሉ ናኝቷል። በፖርቹጋል ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ በእንግሊዝ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ በስፔን በማድሪድ እና በጣልያን በጁቬንቱስ በአስደናቂ ብቃት የተጫወተው ሮናልዶ በዋንጫ ያሸበረቀ ጊዜን አሳልፏል።
በአስደናቂ ብቃቱ ስታዲዬም የሚያሸብረው ሮናልዶ በየሀገራቱ ሊጎች የብቃቱን ጫፍ አሳይቷል። በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ በፍቅር ገብቷል። በእግር ኳስ አያሌ ስኬቶችን አሳክቷል።
ጊዜው ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ የሚጫወትበት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን ሮናልዶ፣ ሪዮ ፈርዲናንድ እና አንደርሰን ባሉበት አንድ ጋዜጠኛ ቀርቦ ለእያንዳንዳቸው የዓለማችን የምንጊዜውም ምርጥ ተጫዋች ማነው? ብሎ ጠየቃቸው። ሪዮ ፈርዲናንድ “ለእኔ የዓለም የምንጊዜም ምርጡ ተጨዋች ዲያጎ ማራዶና ነው” አለ።
ጋዜጠኛው ማይኩን ወደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አዞረ። ማራዶና ወይም ፔሌ ሊል እንደሚችል ተጠብቆ ነበር። ሮናልዶ ግን ያልተጠበቀ መልስ ሰጠ። የዓለም ምርጡ ተጨዋች “እኔ ነኝ” አለ። ጋዜጠኛው እና የቡድን አጋሮቹ ሳቁ። ሮናልዶ የሚደርስበትን አስቦ የሚሠራ፣ ያሰበውን ማሳካት እንደሚችል የሚያምን ተስፋ ያለው ጠንካራ ሠራተኛ ነው።
በጠንካራ ሥራውም ያለውን አሳካ። ከዓለም የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው ኾነ። ይህን ደግሞ ሚሊዮኖች ይመሰክሩለታል።
በዓለም ላይ በማኀበራዊ ሚዲያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማፍራት ቀዳሚ የኾነው እና አያሌ ክብረ ወሰኖችን በብቸኝነት የያዘው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዓመታት በፊት ሲያጸዳቸው የነበሩ ጉዳናዎች ዛሬ ላይ ለእርሱ ክብር ይዘጋሉ። ሳር ቅጠሉ ሁሉ የሚያረግድለት ኾኗል።
ሮናልዶ በአውሮፓ የነበረውን የእግር ኳስ ምዕራፍ ዘግቶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ ካመራ በኋላ ከእግር ኳስ ባሸገር ስሙ ናኝቷል። በሮናልዶ ምክንያት የዓለም የእግር ኳስ ከዋክብት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እያቀኑ ነው። የሳዑዲ አረቢያ ሊግም በሮናልዶ ምክንያት ስሙ ከፍ ብሏል። የሮናልዶ ተጽዕኖ በሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ብቻ የተገደበ አይደለም፣ በቱሪዝም፣ በፖለቲካ በሌሎች ጉዳዮች ጭምር እንጂ።
በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በነጩ ቤተ መንግሥት የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማንን ሲቀበሉ በክብር እንግድነት ከተቀበሏቸው ዝነኞች መካከል ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንደኛው ነበር። ከልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ይልቅ የሚዲያዎችን ቀልብ የሳበውም የክርስቲያኖ ሮናልዶ ጉዳይ ነበር።
ሮናልዶ በተቀናጣው የነጩ ቤተ መንግሥት ያደረገውን የእራት ግብዣ አስመልክቶ ዘገባ ያስነበበው ቢቢሲ ክርስቲያኖ በሳዑዲ አረቢያ ያደረገው አስተዋጽኦ ለሀገሪቱ እንቅስቃሴ ፈታውራሪ እንዲኾን አድርጎታል ብሏል።
የነጩ ቤተ መንግሥት አለቃ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕም ሮናልዶን “አንተን ማስተናገድ ክብር ነው” ብለዋል።
ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ሀገራቸው ሳዑዲ በነዳጅ ገቢ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ወደ ሌሎች የልማት ዘርፎች ፊታቸውን አዙረዋል። ስፖርት እና ቱሪዝም ደግሞ ልዑሉ ትኩረት ካደረጉባቸው ዘርፎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ይህን ዕቅዳቸውን ለማሳካት እና ነገ ላይ ሳዑዲ አረቢያን ገናና የሚያደርጋትን ፕሮጄክት የጀመሩት በክርስቲኖ ሮናልዶ ላይ ነው ይላል ዘገባው።
ሮናልዶ በአውሮፓ የነበረውን የእግርኳስ ምዕራፍ ዘግቶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከሄደ በኋላ ሳዑዲ ሳትነሳ ውላ አድራ አታውቅም። ለወትሮው ስሟን በጥርጣሬ ያነሱት የነበሩ የምዕራባውያን ሚዲያዎች በሮናልዶ ምክንያት በመልካም ነገር ማንሳት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ታዲያ የነጩ ቤተ መንግሥት የእራት ግብዣ ላይ ሮናልዶ ከልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሳልማን ጋር መገኘቱ ነገሩ ከእግር ኳስ ባሻገር እንደኾነ አመላካች ነው ተብሏል። ሮናልዶ ከልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ልዑክ አባል ይሁን አይሁን ባይታወቅም በነጩ ቤተ መንግሥት ግን እንደሚገኝ አስቀድሞ ታውቆ ነበር ይላል ቢቢሲ በዘገባው።
በዓለም ላይ ለእግር ኳስ ተጨዋቾች ተከፍሎ የማያውቅ ደመወዝ እየከፈለች በሀገሯ የያዘችው ሳዑዲ ከምትከፍለው ደመወዝ በብዙ የበለጠ ጥቅም ሰጥቷታል። ሮናልዶ ሳዑዲ ለጀመረቻቸው የስፖርት ፕሮጄክቶች ሁነኛ ሰው ከመኾን ባሻገር ለሳዑዲ አረቢያ መልካም ገጽታ መገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያን እግር ኳስ ብቻ አይደለም የቀየረው። ስሟን እና ዲፕሎማሲዋን ጭምር እንጂ።
ኤም ኤስ ኤን ዲት ኮም የተሰኘ ድኅረ ገጽ የሮናልዶ የነጩ ቤተ መንግሥት ግብዣ ከእግር ኳስ ባሻገር ነው ብሏል። ሮናልዶ በዚያ ሥፍራ የተገኘው እንደ እግር ኳስ ተጨዋች ብቻ ሳይኾን እንደ ዲፕሎማት ጭምር ነው ይላል። በዓመት ረብጣ ገንዘብ የምትከፍለው ሳዑዲ አረቢያ ራሷን ከነዳጅ ኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማውጣት በምታደርገው ሂደት ውስጥ ሮናልዶን ቀዳሚው ሰው አድራጋ እየተጠቀመችበት ነው ብሏል።
የእግር ኳስ ስታዲየሞችን ማንቀጥቀጥ የለመደው ሮናልዶ በነጩ ቤተ መንግሥት የፈጠረው ተጽዕኖም የተለየ ነበር ይላል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ በቤተ መንግሥታቸው ተገኝቶ መነጋገሪያ ለኾነው ኮከብ ልዩ ስጦታ እንደሰጡም ዴይሊ ሜል ዘግቧል። ስጦታው ለጥቂት እና ለልዩ የክብር እንግዶች ብቻ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ወርልድ ሶከር ቶክ የተባለው ድኅረ ገጽ ደግሞ ሮናልዶ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ የነጩን ቤተ መንግሥት ቁልፍ ተቀብሏል ብሏል። ይህን ክብር የሚያገኙት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።
ከጾም አዳሪነት እስከ ነጩ ቤተ መንግሥት የደረሰው የሮናልዶ ዝና የነዳጅ ሃብታሟ ሀገር ሳዑዲ አረቢያ ከዓለም ጋር መልካም ግንኙነት እንድትፈጥር አድርጓታል። አሁን ዓለም ስለ ሮናልዶ እና ስለ ሳዑዲ አረቢያ ዕድገት፣ የቀጣይ ፕሮጄክት በማውራት ተጠምዷል።
ኢ ኤሰ ፒ ኤን በዘገባው በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ ግድያ እጃቸው አለበት ተብሎ በአሜሪካ ሲወነጀሉ የነበሩት ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን በነጩ ቤተ መንግሥት የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል ብሏል። ትናንት እንደ ገዳይ ሲቆጠሩ የነበሩት ልዑሉ ዛሬ ላይ የአሜሪካ ወዳጅ ናቸው። አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያም የጋራ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተስማምተዋል። ለዚህ መልካም ግንኙነት ደግሞ የክርስቲያኖ ሮናልዶ እጅ አለበት ተብሏል።
ቢን ስፖርት በነጩ ቤተ መንግሥት የክርስቲያኖ ሮናልዶ መገኘት ከእግር ኳስ የተሻገረ መልዕክት አለው፤ በዓለም እግር ኳስ ተጨዋቾች ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ሰው መኾኑን አሳይቷል ይላል።
ከዓመታት በፊት በእግር ኳስ ስሟ የማይነሳው ሳዑዲ አረቢያ በሮናልዶ አማካኝነት ስሟ ገናና ኾኗል። የ2034 የዓለም ዋንጫ የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላትም ተገልጿል። ይህ ደግሞ እውን መኾኑ አይቀርም ተብሏል። ለዚህ ደግሞ የሮናልዶ ተጽዕኖ ቀዳሚው ነው።
ሮናልዶ በሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ተጫዋች ብቻ አይደለም። ሳዑዲ አረቢያ በዓለም ሀገራት አምባሳደር አድርጋ የሾመችው አምባሳደር ጭምር ነው እንጂ። በዓለም ሀገራት የተሰጠውን የአምባሳደርነት ኀላፊነትም በአግባቡ እየተወጣ እና ተደማጭነቷን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረውም ይገኛል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



