ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 5:00 ላይ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ከኤቨርተን ይጫወታሉ፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ11 ጨዋታዎች 18 ነጥቦችን በመሠብሠብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ኤቨርተንን 35 ጨዋታ ጋብዞ በ23 ጨዋታ በማሸነፍ እና በ11 ጨዋታ አቻ በመለያዬት የበላይነቱን አስመስክሯል። ኤቨርተን ማንቸስተርን ያሸነፈው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታውን ካሸነፈ ደረጃውን ወደ አምስተኛ ከፍ ማድረግ ያስችለዋል። አራት ግብ እና ከዚያ በላይ አስቆጥሮ ካሸነፈ ደግሞ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትም እድል አለው።
አሠልጣኝ ሩብን አሞሪም ያለመሸነፍ ጉዟችንን ለማስቀጠል እንጫወታለን ብለዋል።
ኤቨርተን በ2025/2026 የውድድር ዘመን ከ11 ጨዋታዎች 15 ነጥብ በመያዝ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የኤቨርተኑ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞይስ ማንቸስተር ዩናይትድ ከጨዋታ ጨዋታ እየጠነከረ የመጣ ቡድን መኾኑን ተናግረዋል። እኛም በቴክኒክ፣ በታክቲክ እና በሥነ ልቦና እየተገነባን በመኾኑ እናሸንፋለን ነው ያሉት።
ኤቨርተንም ድል ከነሳ ደረጃውን የሚያሻሽልበት በመኾኑ ጨዋታው ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል። ቢቢሲ እና ዴይሊ ሜይልን በምንጭነት ተጠቅመናል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



