ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታላላቆቹ ክለቦች በተሸነፉበት ጊዜ ዛሬ ምሽት 1፡30 ላይ ወሳኙን ጨዋታ ከምንጊዜም ተቀናቃኙ ቶተንሀም ሆትስፐር ጋር የሚያደርገው አርሰናል ነጥቡን ያሳካል ወይስ የሌሎቹ እጣ ይደርሰዋል የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡
የ12ኛ ሳምንት የሊጉ ውጤት ለአርሰናል ልዩነቱን የሚያሰፋበት በመኾኑ ለክለቡ እና ደጋፊዎቹ ሰርግ እና ምላሻቸው ነው።
ይህ ደስታ ሙሉ እንዲኾን ግን ክለቡ የዛሬውን የቤት ሥራ በሚገባ ጥንቅቅ አድርጎ መሥራት ይኖርበታል።
የሰሜን ለንደኑ ደርቢ በታሪክ ሁሌም ያልተጠበቁ ክስተቶች የሚበዙበት በመኾኑ ምሽቱ ላይ የአርሰናል ደጋፊም ይሁን ተቀናቃኝ የስፖርቱ አፍቃሪያንን ብድግ ቁጭ የሚያደርግ ጨዋታ ነውና በጉጉት ጨዋታው የሚታይ ይኾናል።
አርሰናል ከቶተንሀም ሆትስፐር በተገናኘባቸው ያለፉት 9 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሰባቱ በአርሰናል የበላይነት የተጠናቀቁ ናቸው። ጉዳዩ አርሰናሎች በሜዳቸው ኤምሬትስ የሚያደርጉትን 212ኛውን ደርቢ ድል ይቀናቸዋል ወይስ ያልጠበቁት ይኾናል ጨዋታው የሚያስመለክተን ነው የሚኾነው።
በሊጉ ውጤታማ እየኾነ የሚገኘው አሠልጣኙ ሚካኤል አርቴታ በዚህ የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጭ ያልተሸነፈውን ብቸኛው ክለብ ቶተንሀም ሆትስፐርን የሚገጥሙ በመኾኑ በብዙ ይፈተናሉ ሲል ቢቢሲ በስፖርት በገጹ አስነብቧል።
ስካይ ስፖርት እንዳስነበበው ደግሞ በመድፈኞቹ በኩል ጋብርኤል ማጋሌሽ በጉዳት አይሰለፍም። ይሁን እንጅ ቦታውን ፒዩሮ ሂንካፔ ይሸፍናል ነው የተባለው።
ሪካርዶ ካላፊዮሪ፣ ቪክቶር ዮኬሬስ፣ ጋብርኤል ማርቲኔሊ፣ ማርቲን ኦዴጋርድ፣ ጋብርኤል ጄሱስ፣ ኖኒ ማዱኬ እና ካይ ሀቨርዝ በአርሰናል በኩል እስካሁን የመሰለፋቸው ነገር ስላልተረጋገጠ የቡድኑ ጥምረት የሳሳ ኾኖ ተስተውሏል፡፡
ጠንካራው እና የመድፈኞቹ ተቀናቃኝ እስካሁን በወጣው መረጃ በተጫዋች አሰላለፍ በኩል የተሻለ እንደኾነ ነው ስካይ ስፖርት ያተተው።
የዛሬው የሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች ጨዋታ ማንን ያነግሳል የሚለው ግን ተጠባቂ ነው የሚኾነው።
ሌላው ዛሬ በሊጉ የሚደረገው ጨዋታ 11፡00 ላይ ሊድስ ከአስቶንቪላ የሚያደርጉት ነው።
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



