የተጫዋቾች ጉዳት ይበልጥ የትኛውን ክለብ ይፈትን ይኾናል?

0
70
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሀገራት ጨዋታ መልስ ቅዳሜ በ12ኛ ሳምንት ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለዋንጫ፣ ለአውሮፓ ውድድሮች ተሳትፎ እና ላለመውረድ የሚደረጉ ትንቅንቆች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ይጠበቃል፡፡
ኦፕታ ስካይ ስፖርትን ዋቢ አድርጎ ባጋራው መረጃ መሠረት 20ዎቹም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በጉዳት ታምሰዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2025/26 የውድድር ዘመን በርካታ ጉዳቶችን ካስመዘገቡ ክለቦች ውስጥ ማንቸስተር ሲቲ በ21 ጉዳት ከፍተኛውን ቁጥር ይዟል፡፡ ሊድስ ዩናይትድ 19፣ (ቼልሲ፣አርሰናል እና ሊቨርፑል) ደግሞ እኩል 18 ጉዳቶችን አስመዝግበዋል፡፡
ያለፈውን ዓመት ያለምንም ዋንጫ ያጠናቀቀው የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ስፔናዊውን የመኻል ሜዳ ሞተር ሮድሪጎን ማጣቱ ለውጤት አልባ ጉዞው በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ኦፕታ በመረጃው አጋርቷል፡፡
ብራዚላዊውን ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከርን በጉዳት ያጣው የአምናው ሻምፒዮና ሊቨርፑል ደግሞ ዘንድሮ የሌሎች ተጨዋቾችን ጉዳት ጨምሮ አርኔ ስሎትን እና ክለባቸውን ከዋንጫ ፉክክሩ እንዳይርቃቸው ሥጋት ኾኗል፡፡
ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በሁለተኛነት ያጠናቀቀው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ዘንድሮ ለዋንጫ ከተገመቱት ክለቦች ውስጥ በቀዳሚነት እንደተቀመጠ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ያም ኾኖ ግን ሚኬል አርቴታ አምበሉን ማርቲን ኦዲጋርድን ጨምሮ በርካታ በቋሚ አሰላለፍ የሚጠቀምባቸውን ተጨዋቾቹን በጉዳት ማጣቱ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ሳንካ እንዳይፈጥርበት ተሠግቷል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ ያለ እንግሊዛዊው ኮከቡ ፖል ፓልመር ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ የጠቀሰው የኦፕታ መረጃ በውድድር ዓመቱ ቼልሲን በውጤታማነቱ ለማስቀጠል የኤንዞ ማሬስካው ሠራዊት ከሌሎች ጉዳቶች መራቅ እንዳለበት ተንብዩዋል፡፡
እንግሊዛዊውን የአማካይ ተጨዋች ማዲሰንን በጉዳት ለረጅም ጊዜ ያጣው ቶተንሃም ሆትስፐር፣ ክሪስታል ፓላስ፣ ብራይተን እና አስቶንቪላም በውድድር ዓመቱ እያንዳንዳቸው 17 ጉዳቶችን አስመዝግበዋል፡፡
ቶተንሃሞች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ዴጃን ኩልሴቪስኪ እና ዶሚኒክ ሶላንኬንም በጉዳት እየተጠቀሙባቸው አይደለም፡፡
ሰንደርላንድ፣ ብሬንትፎርድ እና ኒውካስል ዩናይትድ በውድድር ዓመቱ 13 ጉዳቶችን፣ ፉልሃም 12፣ (በርንሌይ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት እና ኤቨርተን) እያንዳንዳቸው 11 ተጨዋቾች፣ በርንማውዝ እና ዌስትሃም ደግሞ 10 ጉዳቶችን አስመዝግበዋል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትዶች ስምንት ጉዳት ያስመዘገቡ ሲኾኑ ከአውሮፓ ጨዋታ ውጪ በመኾናቸው ለወደፊቱ ብዙም የጉዳት ዜና እንደማይኖርባቸው ስካይ ስፖርት ገምቷል፡፡ ቀያይ ሰይጣኖቹ የፊት መስመር ተሰላፊያቸውን ቤንጃሚን ሴስኮን ጨምሮ የተጎዱ ተጨዋቾች ቢኖሩም ከሁሉም ክለቦች የተሻለው ጉዳት የተመዘገበው በእነሱ ነው፡፡
ተጨዋቾችን በጉዳት ምክንያት ለረጅም ቀናት ባለማሰለፍ ደግሞ ቶተንሃም ሆትስፐር በ516 ቀናት ቀዳሚው ክለብ ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ ሰንደርላንድ፣ ክሪስታል ፓላስ፣ ቼልሲ፣ ብራይተን፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል፣ በርንሌይ፣ ሊቨርፑል እና አስቶን ቪላ ደግሞ ከሁለተኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ በሚደረጉ 10 ጨዋታዎች ይመለሳል፡፡ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ሦስት ወሳኝ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾቹን ጋብርኤል ማጋሌሽ፣ ሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ጁሪያን ቲምበርን በጉዳት ያጣው መሪው አርሰናል ከቶተንሃም ሆትስፐር ጋር የሚያደርጉት የሰሜን ለንደን ደርቢ ጨዋታ በ12ኛ ሳምንት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ለመኾኑ የተጨዋቾች ጉዳት ይበልጥ የሚፈተነው ክለብ የቱ ነው ይላሉ? የትኞቹ ክለቦችስ በፈተናዎች ውስጥ አልፈው ለስኬት ይበቃሉ?
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here