ባሕር ዳር: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ካናዳ፣ ሜክስኮ እና አሜሪካ በጥምረት ያዘጋጁታል። በዚህ 23ኛው የዓለም ዋንጫ 48 ሀገራት ተሳታፊም ይኾኑበታል፡፡
ከአፍሪካ ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ኮትዲቯር፣ ቱኒዚያ፣ ጋና፣ አልጀሪያ እና ሞሮኮ በየምድባቸው ያደረጉትን የማጣሪያ ጨዋታዎች በአንደኛነት በማጠናቀቅ ለዓለም ዋንጫ ጨዋታ ማለፋቸው ይታወቃል፡፡
ምርጥ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የፈጸሙት አራት የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ለኢንተርኮንቲኔንታል ጥሎ ማለፍ ለመድረስ ናይጀሪያ ጋቦንን 4 ለ1 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካሜሩንን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዛሬው የመጨረሻ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡
ጨዋታው በሞሮኮ ራባት ከተማ በሚገኘው በስታድ ልዑል ሄሪቲየር ሙላይኤል ሀሰን ስታዲየም ይደረጋል፡፡
አሸናፊው ብሔራዊ ቡድን በመጋቢት ወር በሀገረ ሜክስኮ ከሌሎች አኅጉራት በምርጥ ሁለተኛነት ከተውጣጡ ሀገራት ጋር በኢንተር ኮንቲኔንታል ጨዋታ በመፋለም ድል አድራጊው በዓለም ዋንጫ ተሳታፊ እንደሚኾን ነው ካፎ ኦን ላይን ዶት ኮም ያስነበበው፡፡
ናይጀሪያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ሦስት ላይ ተደልድላ 10 ጨዋታዎችን አድርጋለች። በአራት ጨዋታዎች አሸንፋ በአምስቱ አቻ ተለያይታ እና በአንዱ ተሸንፋ 17 ነጥብ በመያዝ በምርጥ ሁለተኛነት አጠናቃለች።
የሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በሻምፒዮንስ ሊጉ በሦስት ጨዋታዎች ብቻ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የወቅቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የኾነው ቪክቶር ኦሲምሄን እና የቡድን አጋሮቹ ግብ የማስቆጠር ብቃታቸው ከፍተኛ መኾኑ እየተነገረ ይገኛል።
ምድብ ሁለት ላይ 10 ጨዋታዎችን ያደረገችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሰባት ጨዋታዎች አሸንፋ፣ በአንዱ አቻ ተለያይታ እና በሁለት ጨዋታዎች ተረትታ 22 ነጥብ በመሰብሰብ በምርጥ ሁለተኛነት በማጠናቀቅ እና “ኃያል” የተባለውን ካሜሩንን 1ለ0 በመርታት ነው ለዛሬው ጨዋታ የደረሰችው፡፡ ይህም የቡድኑን ብርታት ያመላክታል ተብሏል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በተለይ የመከላከል አቅም ከናይጀሪያ የተሻለ መኾኑንም ነው ሬቲንግ ቢት በድረ ገጽ ያስነበበው።
ናይጀሪያ (ሱፐር ኤግልስ ) እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (ሊዎፓርድስ) ከ1966 ጀምሮ በስድስት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍም የበላይነቷን አሳይታለች። በአንጻሩ ናይጀሪያ በሁለት ግጥሚያዎች ድል አድርጋለች፤ በአንድ ጨዋታ አቻ መለያታቸውን ያሁ ስፖርት አስነብቧል፡፡
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመከላከሉ፤ የናይጀሪያ ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ብልጫ ስለሚኖራቸው ጨዋታው ከባድ እንደሚኾን ነው የተገለጸው።
ጨዋታው ምሽት 4:00 የሚደረግ ሲኾን የ38 ዓመቱ ሞሮኳዊ ጃላል ጄይድ እንዲዳኙት በፊፋ ተመርጠዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



