አዲስ አበባ: ኅዳር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ በኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ስም የተሰየመውን ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
መንግሥቱ ወርቁ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ታሪክ እና ዝና ካላቸው ተጨዋቾች መካካል ናቸው። በተለይ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1962 ኢትዮጵያ ባስተናገደችው እና አሸናፊ በኾነችበት የአፍሪካ ዋንጫ በተጫዋችነት ታሪክ የሠሩ የምንጊዜም የእግር ኳሱ ጀግና ናቸው።
በወቅቱ የውድድሩ ኮኮብ ተጨዋች በመኾንም ተመርጠው ነበር። እስካሁንም ይህን ክብር ያገኙ ብቸኛው ተጨዋች ናቸው።
መንግሥቱ ወርቁ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጨማሪ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከ10 ዓመታት በላይ ተጫውተዋል። በርካታ ክብሮችንም አሳክተዋል። ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም እሳቸው ይለብሱት የነበረውን ማልያ በክብር አስቀምጧል።
የአቢሲኒያ ባንክ የደምበኞች ሒሳብ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አየለ ገብሬ አቢሲኒያ ባንክ ለሀገር የሠሩ እና ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸውን ግለሰቦች በማክበር እና በመዘከር ይታወቃል ብለዋል። በሀገር ደረጃ ካሉን ቅርንጫፎች መካከል ግማሽ ያህሉ በሀገር ባለውለታዎች እና ታሪክ በሠሩ ግለሰቦች ስም የተሰየሙ ናቸው ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሕያው አሻራ ባላቸው ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ስም ቅርንጫፍ መክፈት ለባንኩ ግዴታም፤ ክብርም ነው ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ ይህን በማድረጋችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
አቢሲኒያ ባንክ በቀጣይም ለሀገር የሠሩ ታላላቅ ሰዎችን ለማሰብ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የእግር ኳሱን ሕያው ባለታሪክ ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁን ለማሰብ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን በቀለ
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የጎላ አሻራ ከነበራቸው የኳስ ሊቆች ውስጥ አንዱ የኾኑት መንግሥቱ ወርቁ የእግር ኳስ ታሪካቸው በመጽሐፍ ተጽፎ ሊመረቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
ኅዳር 14/2018 ዓ.ም በሰለሞን በርሄ (ዶ.ር) የተጻፈ “መንግሥቱ ወርቁ የእግር ኳስ ዕንቁ” የተሰኘ መጽሐፍ እንደሚመረቅም ተመላክቷል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው አቢሲኒያ ባንክ መንግሥቱ ወርቁን በማሰቡ ክብር እንደተሰማቸው ተናግረዋል። የቀደሙ ታሪክ ሠሪዎችን ማሰብ እና መዘከር የዛሬን ትውልድ የሚያበረታ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮነን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



