አጼዎቹ ከመቻል የሚያደረጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በሀዋሳ

0
66
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ዛሬ አራት መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ።
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከልም የሊጉ ጠንካራ ክለቦች ፋሲል ከነማ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በሊጉ የመሪነት ስፍራን ይዘው የሚገኙት እነዚህ ክለቦች ከአራት ጨዋታ በአንድ ጨዋታ ብቻ አቻ በመለያየት እና በሊጉ ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ጠንካራ መኾናቸውን ያሳዩ ክለቦችም ናቸው
አጼዎቹም ኾነ መቻል ዛሬ የሚያደርጉትን ጨዋታ በማሸነፍ አሁን ካሉበት 10 ነጥብ ወደ 13 ነጥብ በማሳደግ በሊጉ የተሻለ ቦታ ላይ ለመቀመጥ ሲሉ ነው ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቀው።
ከዚህ በፊት በነበሩ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናን እና ምድረገነት ሽረን 1ለ0 እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2ለ0 ማሸነፍ የቻለው ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ1 ነው የተለያየው።
መቻል በበኩሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ1፣ ወላይታዲቻን 1ለ0 እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር ደግሞ 2 አቻ ነው የተለያዩት።
አጼዎቹ እስካሁን መረባቸው የተደፈረው አንድ ጊዜ ብቻ ሲኾን መቻሎች ደግሞ ሦስት ጊዜ መረባቸው ተደፍሯል።
ግብ በማስቆጠር በኩል መቻል 8 ኳሶችን መረብ ላይ በማሳረፍ የተሻለ ሲኾን አጼዎቹም አምስት ጊዜ ያህል የተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ላይ ደረሰው ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ሁለቱ ከለቦች ዛሬስ ያላቸውን የበላይነት ለማሳየት በሚያደርጉት ጨዋታ ማን ያሸንፋል የሚለው የሚጠበቅ ነው የሚኾነው። ሁለቱ ቡድኖችም 12፡00 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሊጉ ሌሎች ጨዋታዎችም ሲደረጉ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና 7፡00 ላይ፤ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 9፡00 እና ሸገር ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና 10፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here