አዲስ አበባ: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 17ኛው መደበኛ ጉባኤ እንደቀጠለ ነው።
ከሰዓት በኋላ በቀጠለው መርሐ ግብር የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ተደርጓል። በዕቅዱ ዙሪያም ተሳታፊዎች ሃሳብ ሰጥተውበታል።
ወጣቶች ላይ የሚሠሩ ተግባራትን አጠንክሮ ማስቀጠል፣ የብሔራዊ ቡድን ውጤትን ማሻሻል፣ የክለብ ላይሰንሲንግ፣ የአሠልጣኞችን ብቃት ማሻሻል እና የስፖርት ማዘውተሪያ ተግባራትን በተመለከተ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል።
የአሠልጣኝነት ሥልጠና እና ምዘናን በተመለከተ በጉኤው ተሳታፊዎች ጥያቄ ተነስቷል። በጉባኤው “የአሠልጣኞች ሥልጠና እና የምዘና ጥራት አጠያያቂ ናቸው” በሚል ለተነሳው ሃሳብ ምላሽ የሰጡት የሥልጠና እና ምዘና ቋሚ ኮሚቴ አባል ኢሊት ኢንስትራክተር አብርሐም መብራቱ ናቸው።
ኢትዮጵያ የ ዲ ላይሰንስ አሠልጣኞችን ላይሰንስ በመስጠት ከአፍሪካ ምርጥ ሀገራት ውስጥ እንደምትገኝ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የፋስት ትራክ ሥልጠና በመስጠትም ከሞሮኮ ቀጥላ የምትጠቀስ ሀገር ናት ብለዋል ኢንስትራክተር አብርሐም መብራቱ።
ኢትዮጵያ የኤ ላይሰንስ ሥልጠናወችንም በመስጠት ጥሩ ተሞክሮ ያላት ሀገር ናት ያሉት ኢንስትራክተር አብርሐም ሥልጠናው በንድፈ ሃሳብ፣ በተግባር እና በጨዋታ አመራር ያላቸውን ብቃት ገምግሞ እና መዝኖ ነው ላይሰንስ የሚሰጠው ብለዋል::
ጉባኤው በመጨረሻም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድን ገምግሞ አጽድቋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



