ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
በእግር ኳስ ጨዋታ ዳኛ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም በርካታ ተጫዋቾች ዳኛን በመክበብ ሲያዋክቡ እና ሲጨቃጨቁ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ዳኛው ተረጋግቶ ውሳኔ እንዳይሰጥ የሚኖረው ጫና እና ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ችግሩን በአንክሮ የመረመረው የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርም ዳኛን ከበባ ውስጥ አስገብቶ የማዋከብ ድርጊትን ያስቀራል ያለውን ሕግ ይፋ አድርጓል።
በጀርመን በሚደረገው ዩሮ 2024 ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በዳኛ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በመቃወም ወደ ዳኛ ቀርበው ቅሬታቸውን እንዲናገሩ የሚፈቀድላቸው ተጫዋቾች አምበሎች ብቻ እንደኾኑ ተደንግጓል። የእግር ኳስ ማኅበሩ የዳኞች ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሮቤርቶ ሮዜቲ እንዳሉት በጨዋታ ወቅት በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ ዳኛን የሚያናግር ብቸኛው ተጫዋች አምበሉ ብቻ ነው። ስለኾነም አምበሎቹ የቡድን አጋሮቻቸው ዳኛውን ለማናገር እንዳይሞክሩ አስቀድመው ሊመክሩ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።
አንድ ተጫዋች ወደ ዳኛው ተጠግቶ ካወራ ወይም ምልክት የሚያሳይ ከኾነ በቢጫ ካርድ እንዲቀጣ ሕጉ ደንግጓል ሲል ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል። አምበሉ ግብ ጠባቂ ከኾነ እርሱን ተክቶ ሚናውን የሚወጣ ተጫዋች ተለይቶ ለዳኛው ሊነገረው ይገባልም ተብሏል። የዩሮ 2024 ዋንጫ በጀርመን አሰተናጋጅነት ሰኔ ላይ ይጀምራል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!