“የባሕል ስፖርትን የአማራ ክልል መለያ ለማድረግ ይሠራል” የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ

0
245

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት ሙላት ገረመው ባሕላዊ የገበጣ ስፖርት ተጫዋች ነው። ወጣቱ እንደሚለው በትምህርት ቤት የመውጫ እና የመግቢያ ሰዓት እስኪ ደርስ ዛፍ ጥላ ሥር ጉድጓድ አዘጋጅተው ይጫወታሉ። በትምህርት ቤት ጅማሮውን ያደረገውን የገበጣ ጨዋታ ከትምህርት ቤት መልስም አልፎ አልፎ በአካባቢው ከጓደኞቹ ጋር በመጫወት ልምዱን እንዳዳበረው ነግሮናል።

” አንዳንድ ሰዎች ገበጣ ስንጫዎት ሲያዩ ሥልጣኔ ያልገባችሁ” በማለት ለማፌዝ ይሞክራሉ ፤ እነርሱ ግን መውቀስ የነበረባቸው የእግር ኳስ ጨዋታን የመወራረጃ ቁማር ያደረጉትን አለን። ሙላት እንደሚለው አሁን ላይ ገበጣን በትምህርት ቤት አካባቢ መጫዎት እምብዛም የሚበረታታ ኾኖ አላገኘውም። ምናልባትም አንዳንዶች እንደሚሉት ያለ መሠልጠን ምልክት ተደርጎ በመወሰዱ ሳይኾን አይቀርም ይላል። ስለዚህ ትምህርት ቤቶች ለባሕል ስፖርት ዓይነቶችን ትኩረት ቢያደርጉ ስፖርቱ እንዳይደበዝዝ የማድረግ ጉልበት አላቸው እንደ ወጣቱ ሀሳብ።

ሌላዋ ሀሳብ የሰጠን ፈረስ ጋላቢ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪው ብርሃነመስቀል ተረፈ ይባላል። በእነርሱ አካባቢ ፈረስን ከመጓጓዥ ባለፈ በበዓላት ወቅት እርስ በርስ ይወዳደሩበታል። በዓመት አንድ ጊዜም ፈረሰኞች እየተመረጡ ለውድድር ይሄዳሉ ነው ያሉት። “የፈረስ ግልቢያን እንደ አንድ የስፖርት ዓይነት ቆጥሮ ሥልጠና እያመቻቹ በየጊዜው ማወዳደር ቢቻል አንድም ዘርፉን ማስቀጠል ሁለትም ከቀበሌ ባለፈ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሀገር ገጽታ መገንቢያ ማድረግ ይቻላል” ብሏል ወጣት ብርሃነመስቀል።

የስፖርት ሳይንስ መምህር ባይህ ከበደ እንደሚሉት በኢትዮጵያ አብዛኛው የገጠር አካባቢ ከታኅሳሥ ወር ጀምሮ አርሶ አደሩ አዝመራውን ስለሚሸክፍ እንዲሁም ሜዳው ነጻ ስለሚኾን ገና ለመጫዎት፣ ፈረስ ለመጋለብ የተመቼ ነው። ገበጣ እና ቡብን በተመለከተ ሁለት እና ከዚያ በላይ የኾኑ ሰዎች መጫዎት ስለሚችሉ ከእረኞች እስከ ተማሪዎች እንዲያዘወትሩት ማድረግ ቀላል ነው። በተጨማሪም የጦር ውርወራን የመሳሰሉ የባሕል የስፖርት አይነቶችን በትምህርት ቤት አካባቢ ማስፋፋት ይቻላል ብለዋል።

ባሕላዊ ስፖርትን በማስፋፋት ከሥልጣኔ እና ዘመናዊነት ጋር በተያያዘ ትውልዱ ማንነቱን እንዲያውቅ እና ባሕሉን እንዲያሳድግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው:: መፍትሔው ደግሞ እንደ እግር ኳስ ሁሉ ዓመቱን ሙሉ የባሕላዊ ስፖርቶች ውድድሮችን ከቀበሌ እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ በማካሄድ ችግሩን ማስወገድ ይቻላል ብለዋል መምህር ባይህ።

መምህሩ አክለውም ውድድሮች ሲኖሩ ደግሞ ሕዝቡ ባሕልን ከመግለጽ ባለፈ ትውፊቱን አንዱ ለሌላኛው አካባቢ በማስተዋወቅ የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማሳደግ ሰላምን ለማስፈን የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው እና መንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ በመሥራት ሚሊዮኖች ጋር መድረስ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ጋሸው ተቀባ ክልሉ በችግር ውስጥ ኾኖም በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በ11 የስፖርት ዓይነቶች በተደረገው 21ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር ዘጠኙን በማሸነፍ እና የፀባይ ዋንጫ በመሸለም በድምሩ በ10 የስፖርት ዓይነቶች ሻምፒዮን በመኾን ክልሉ በበላይነት አጠናቅቋል።

ለውጤቱ መገኘት ደግሞ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ዞኖች ከቀበሌ ጀምሮ ዓመቱን ሙሉ ውድድሮች መደረጋቸው ነው ብለዋል፤ ዋግ ኽምራ ደግሞ በአርዓያነት ይጠቀሳልም ብለዋል። በየዞኖችም በተደረጉ ውድድሮች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞችን በመለየት በተሻለ አሠልጣኝ፣አስተባባሪ፣ የቴክኒክ መሪ በጥሩ ቅንጅት ሥልጠና መሰጠቱ አሸናፊ አድርጎናል ነው ያሉት።

ኀላፊው አክለውም “ክልሉ ቀውስ ውስጥ በመቆየቱ በውድድሩ የመሳተፍ አቅም የላቸውም” የሚሉን ቢበዙም እኛ ግን በጥሩ ዝግጅት ተሳትፈን አሸናፊ ለመኾን በቅተናል ሲሉ ተናግረዋል። የባሕል ስፖርት በተለይ፦ ፈረስ፣ትግል፣ ዒላማ ተኩስ፣ ገና… ለአማራ ሕዝብ ባሕሉ ነውና ብለዋል። እንደ ኀላፊው ገለጻ የባሕል ስፖርትን ተደራሽ አድርጎ በብዛትም በውጤትም ልቆ ለመገኘት ጥናት ላይ በመመርኮዝ ትምህርት ቤቶች ጋር መሥራት ግድ ይለናል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አብረውን እንዲሠሩ እናደርጋለን። ይህን በማድረግ የባሕል ስፖርትን የአማራ ክልል ብራንድ/መለያ/ እንዲኾን በቅርቡ የተደረገው ፌስቲቫል አሳይቶናል እና ተግተን በመሥራትም እንተገብረዋለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here