ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዛሬን አያድርገውና የማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ተቀናቃኝነት ለእግር ኳስ አፍቃሪያን ልብን የሚያሞቅ ነበር። መጀመሪያ በሞሪንሆው ቼልሲ አሁን ደግሞ በጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ የበላይነታቸውን ከመነጠቃቸው በፊት ሁለቱ ቡድኖች የእንግሊዝ ኅያል የኾኑባቸው ዓመታት የቅርብ ጊዜያት ትዝታ ናቸው።
በፕሪምየር ሊጉ እስከመጨረሻው ተናንቀው የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ልብን ገዝተዋል፤ ከአሠልጣኝ እስከ ተጫዋች፣ በእንግሊዝ ብቻ ሳይኾን በዓለም ላይ ያሉ ደጋፊዎቻቸው ተዘላልፈዋል፤ አልፈውም ለጸብ ተጋብዘዋል። ሰር አሌክስ ፈረጉሰን ከአርሰን ቬንገር፣ ሮይኪን ከፓትሪክ ቬራ፣ እንደቡድን ዩናይትድ ከአርሰናል መሸነፍ የሞት ያህል ተቆጥሮ ለዓመታት የእንግሊዝ ኳስ ድምቀት ኾነው ቆይተዋል።
አሁን ሁለቱ ቡድኖች ከግርማቸው ከወረዱ ዓመታት ተቆጥረዋል። የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነትም እንደበፊቱ በመላው ዓለም የሚናፈቅ ከመኾን ወርዶ ተራ መርሐ ግብር እየመሰለ መጥቷል። ዛሬ ሁለቱ ቡድኖች በኦልድ ትራፎርድ ሲጫወቱ ግን ጨዋታው የሚጠበቅበት በቂ ምክንያት አለው።
አርሰናል ከተረሳበት ተነስቶ ለዋንጫው እየተንደረደረ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በማይክል አርቴታ ስር የተሻሻሉት መድፈኞቹ ለውጣቸውን ተጨባጭ ለማድረግ ዋንጫ ያስፈልጋቸዋል። ለፕሪምየር ሊጉ ክብር ከሲቲ ጋር እስከ መጨረሻው ለመፋለምም ዛሬ ኦልትራፎርድ ላይ ስህተት አይፈቀድላቸውም።
ከአርሰናል በተቃራኒ የኋሊት ጉዞ ላይ የሚገኘው የድሮ አንበሳ ዩናይትድ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ይገኛል። ከፈርጉሰን በኋላ ወደ ክብሩ የሚመልሰው አለቃ ያላገኘው ክለቡ አሁንም በቴንሀግ እርግጠኛ አይደለም። አሠልጣኙ ባለፈውም ዓመት ጥሩ ተስፋ ቢያሳዩም ዘንድሮ ሁሉም ነገር ግራ ኾኖባቸዋል። እንደ ቢቢሲ መረጃም የሰውየው የኦልድ ትራፎርድ እህል ውሀ ወደ መጠናቀቁ ነው።
ዛሬ ከአርሰናል ጋር የሚያስመዘግቡት ውጤትም በሥራቸው ላይ ለተነሳው እሳት ቤንዚን አሊያም ውኃ በመኾን የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። በተጨማሪም ዩናይትድ በአውሮፓ መድረክ ቀሪ ተስፋውን ለመሞከር የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታው ነው። አርሰናል የዋንጫ ግስጋሴውን ለማስቀጠል፣ ዩናይትድ ደግሞ በአሠልጣኙ ላይ እየተነሳ ያለውን ትችት ለማብረድ እና መጥፎ ግስጋሴውን ለጊዜውም ቢኾን ለመርሳት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ በሚል ቀጠሮ ይዘዋል።
ታሪክ ኦልድ ትራፎርድ ለአርሰናል አይመቸውም ይላል። በአርሰናል ይፋዊ ገጽ መረጃ መሰረት አርሰናል ባለፉት 31 የኦልድ ትራፎርድ ጨዋታዎች ድል የቀናው በአራቱ ብቻ ነው። ይህም አርሰናል ከየትኛውም ተጋጣሚው በላይ ለዩናይትድ እጅ እንደሚሰጥ ማሳያ ነው። ነገር ግን በዛሬው ጨዋታ አርሰናል የተሻለ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቶታል። በዓመቱ ያሳየው ወጥ አቋም፣ የዩናይትድ ጥሩ አለመኾን እና የማንቸስተሩ ክለብ በጉዳት መታመስ ለአርሰናል አሸናፊነት መታጨትም ምክንያት ተብለዋል። የተረሳው ተቀናቃኝነት ከእንግሊዝ ባለፈ በሀበሻ ምድርም ምሽት 12:30 ኦልድ ትራፎርድ ላይ የዚያ ዘመን ተቀናቃኝነት እየተናፈቀ በብዙ ይጠበቃል። ታዲያ የዛሬው የኦልድ ትራፎርድ አሸናፊ ማንቸስተር ዩናይትድ ወይስ አርሰናል?
ግምትዎን ያጋሩን። ቀድሞ ትክክለኛ ግምት በቀጣዩ የቴሌግራም ገጽ ላይ በመሞከር ተሸላሚ ይሁኑ።
https://t.me/AmharaMassMedia/37880
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!