በዌምብለይ የዶርትመንድ ተፋላሚ ሪያልማድሪድ ወይስ ባየርሙኒክ?

0
281

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቦሩሲያ ዶርትመንድን አንግሶ ፒኤስጂን አንገት ያስደፋው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽትም ይቀጥላል። ሪያል ማድሪድ እና ባየር ሙኒክም አንዳቸው የዶርትመንድን ሌላቸው ደግሞ የፒኤስጂን እጣ ፋንታ ሊጋሩ ምሽቱን ሲያንቲያጎ ቤርናቦ ቀጠሮ ይዘዋል።

በመጀመሪያው ዙር ጀርመን ላይ ሁለቱ ኃያላን ሁለት አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። ይህ ውጤት ዛሬ በሜዳው ለሚጫወተው እና በውድድሩ ግርማው ለሚያስፈራው ሪያል ማድሪድ የተሻለ ነው እየተባለ ነው፤ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ ለማሸነፍ አይቸገርም በሚል ግምት። ነጮቹ የላሊጋ ዋንጫ ባለቤትነታቸውን ማረጋገጣቸውም ሌላ የምሽቱ ጨዋታ ጉልበት ይኾናቸዋል።

ነገር ግን ዓመቱን ያለዋንጫ ላለማጠናቀቅ የሞት ሽረት ፍልሚያ ያደርጋሉ። ቡድኑ እንደማድሪድ ባይኾንም በሻምፒዮንስ ሊጉ ውጤታማ ታሪክ አለው። እስካሁንም ስድስት ጊዜ ዋንጫውን ማንሳቱን የቶክ ስፓርት መረጃ እማኝ ነው። ሁለቱ ክለቦች የፍጻሜ ቦታን ለማግኘት ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

የሪያል ማድሪዱ አሠልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ ባየር ሙኒክ ታላቅ ክለብ ነው፤ በመጀመሪያው ዙር ከእኛ ተሽለው ተጫውተዋል የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። የላሊጋ ዋንጫ ድላቸውን በደመቀ ኹኔታ ያላከበሩት ማድሪዶች ይኽን ለማድረግ ጊዜው አሁን አይደለም ብለዋል አሠልጣኙ። በሌላ ድል ለመድመቅ ሁለት ጨዋታ ብቻ ይቀረናል የሚል ሃሳብም ጨምረዋል። ይኽ ሪያል ማድሪድ ነው እተማመናለሁ፤ እናደርገዋለንም ሲሉ የዛሬውን ጨዋታ ብቻ ሳይኾን ዋንጫውን እንደሚያነሱ ተናግረዋል።

ባየር ሙኒኮች ዛሬ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ከወጡ ዓመቱን ያለዋንጫ ማጠናቀቃቸው እውን ይኾናል። በዛሬው ጨዋታ ማድሪድን አሸንፈው ከሌላኛው የጀርመን ክለብ ዶርትመንድ ጋር ለፍጻሜ ለመቅረብም ተስፋ ሰንቀዋል። ለዚህም የእንግሊዛዊ አጥቂ ሀሪ ኬን ብቃት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። አጥቂው ክለቡን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ዓመት እስካሁን 44 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ነገር ግን ክለቡ ደካማ የውድድር ዓመትን እያሳለፈ ነው። ይህም ከቡንደስሊጋው እና ከጀርመን ዋንጫ ውጭ እንዲኾን አድርጎታል።

እንደ ቀድሞው የባየርሙኒክ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አማካኝ ሀርግሪቭስ ሃሳብ ከባየር ሙኒክ የዘንድሮ ደካማ ጉዞ አጥቂው ኬን ከደሙ ንጹህ ነው። ክለቡ በትላልቅ ጨዋታዎች ወጥነት ያለው አቋም አለማሳየቱን ያነሳው እንግሊዛዊ የቀድሞ ተጫዋች ሀሪ ኬን ግን የሚጠበቅበትን ኹሉ አድርጓል። ኬን ከሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጭ የሚቀናበት ሰብእና ባለቤት ነው ሲልም ገልጾታል። የዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በዌምብለይ የሚካሄድ ሲኾን የጀርመኑ ዶርትመንድ ቀዳሚው ቲኬት ቆራጭ ኾኗል። ጥያቄው በዌምብሌይ የቢጫ እና ጥቁር ለባሾቹ ተጋጣሚ ሪያል ማድሪድ ወይስ ባየርሙኒክ? መልሱን ፍለጋ ምሽት 4 ሰዓት ስፔን ሎስብላንኮዎቹ ሲያንቲያጎ ቤርናቦ ላይ የእግር ኳስ አፍቃሪያን የማይቀርበት ቀጠሮ ይዘዋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here