የፒኤስጅ አብዮት መጨረሻ!?

0
216

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሰን ዠርሜ በቅርብ ዓመታት የአውሮፓ ክለቦች ኃያል ለመኾን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። በተለይ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያስገኙልኛል ያላቸውን ተጫዋች እና አሠልጣኞች ተዝቆ በማያልቀው የኳታር ከበርቴዎች ገንዘብ እያማለለ ሠብስቧል።

ከተጫዋቾች ሊዮኔል መሲ፣ ነይማር ጁኔር፣ እና ሰርጅዮ ራሞስን የመሳሰሉ ኮከቦች ትልቁን ዋንጫ ከፓሪሱ ክለብ ጋር እንዲያስታርቁ ረብጣ ገንዘብ እያፈሱ ለዓመታት ተሞክረዋል። ነገር ግን አንዳቸውም ክለቡ የፈለገውን ዋንጫ ሳያሳኩ አሁን ከክለቡ ተለያይተዋል። ካርሎ አንቾሎቲ፣ ማውሪዮ ፖችቲንሆ፣ ቶማስ ቱሸልን የመሳሰሉ ስመ ጥር አሠልጣኞች ደግሞ በአሠልጣኝነት እምነት ተጥሎባቸው ግን በፈተናው የወደቁ ናቸው።

በፈረንሳይ ሊግ አንድ በተደጋጋሚ የበላይነቱን ያሳየው ከበርቴው ክለብ ኮከቦችን መሠብሰቡ አጥብቆ የፈለገውን ሻምፒዮንስ ሊግ ግን ሊያስገኝለት አልቻለም። ከክለቡ ጋር በመጭው ክረምት በሚለያየው ኪሊያን ምባፔ ምትሀት ሻምፒዮንስ ሊጉን ከፍ ለማድረግ የነበረው ተስፍም መንገድ ላይ ቀርቷል።

በዚህ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ፒኤስጅ በተለይ በሩብ ፍጻሜ በባርሴሎና በሜዳው ተሸንፎ ውጤት ቀልብሶ ወደ ቀጣይ መሻገሩ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል። በግማሽ ፍጻሜ ብዙ ግምት ካላገኘው ቦሩሲያዶርትመንድ መገናኘቱም እንደጥሩ እድል ተቆጥሮለት ነበር።

ነገርግን ፒኤስጅ እና ኪሊያን ምባፔ ዶርትመንድ እንደባርሴሎና አልቀለላቸውም። የጀርመኑ ክለብ በታታሪ የቡድን አንድነት እና በአስደማሚ ደጋፊዎቹ በመታገዝ እንደክለብ ፒኤስጅን፣ እንደተጫዋች ደግሞ ምባፔን አሸንፈዋል። በደረሶ መልሱ ጨዋታ ሁለቱን ማሸነፋቸው ደግሞ ከጨዋታ በፊት የተሰጣቸው ዝቅተኛ ግምት ትክክል ላለመኾኑ ማሳያ ኾኗል።

ይህን ውጤት ተከትሎ የፒኤስጅ አብዮት ተጠናቀቀ ሲል ቢቢሲ አስነብቧል። ባለፉት ዓመታት ዣላታን ኢብራሃሞቪች፣ ነይማር፣ መሲ እና ሌሎች ኮከቦችን የሠበሠበው ክለቡ ከሊግ ዋንጫ ውጭ በአውሮፓ ያገኘው ክብር የለም። በቀሪ ኮከቡ ምባፔ የነበረው ተስፉም አልተሳካም። ቀጣይ የክለቡ መንገድም የተለየ ይመስላል። ባለፉት ዓመታት ገንዘብ የፈለገውን ተጫዋች እንዲያስፈርም፣ የተመኘውን አሠልጣኝ እንዲቀያይር አግዞታል። ነገርግን በብዙ የተራበውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አላስታገሰለትም።

ከክለቡ በሚወጡ ታላላቅ ተጫዋቾች ምትክ አሁን ኮከቦችን እንደበፊቱ እየሠበሠበ አይደለም።አንደቢቢሲ መረጃም ክለቡ በብዙ ገንዘብ ተጫዋቾች ከማዛወር ይልቅ ታዳጊዎች ላይ እና ራሳቸውን አግዝፈው በማይመለከቱ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት እያደረገ ነው። ምናልባት ይሄኛው መንገድ ያዋጣው እንደኾነም በቀጣይ የሚታይ ይኾናል። ለጊዜው ግን የመጣበትን መንገድ ትክክል አለመኾን ያመነ ይመስላል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here