ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውጤት ቀውስ፣ በአጨዋወት መዋዥቅ፣ በክብሩ ልክ አለመገኘት፣ የአሸናፊነት ስሜቱን መነጠቅ የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን ትዕግሥት አሳጥቷል፡፡ በግሌዘር ቤተሰቦች ስር ኾኖ እግርኳሳዊ ክብሩን ያጣው ማንችስተር ዪናይትድ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመለስ ዘንድ ለውጥ ያስፈልገዋል የሚል ሀሳብ ከደጋፊዎች እና ከቀድሞ ተጫዋቾች ሲነሳ ከርሟል፡፡
የግሌዘር ቤተሰቦች ከሜዳ ውጭ ላለው ትርፍ እንጂ ለእግርኳሳዊ ውጤት፣ የሜዳ ክብር፣ በዋንጫ መታጀብ፣ የተጨዋቾች ምልመላ እና ግዢ ደንታ የላቸውም በሚል ሲከሰሱ ኖረዋል፡፡ ከሰር አሌክስ ፈርጉስን አሠልጣኝነት በጡረታ መልቀቅ በኋላ የማንችስተርን ኀያልነት ማስቀጠል የቻለ አሠልጣኝ አለመገኘቱ ደግሞ ሌላው ሕመም ኾኖ ቆይቷል፡፡
በማንችሰተር ዪናይትድ መልማዮች እየተመለመሉ ረብጣ ገንዝብ እየፈሰሰባቸው ኦልድትራፎርድ የሚደርሱ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከትርፋቸው ይልቅ ኪሳራቸው ማመዘኑ የክለቡን ወዳጆች አበሳጭቷል፡፡ የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን ያልተቋረጠ ውጡልን አመጽ ያልተቋቋሙት የግለዜር ቤተሰቦች ክለቡን ለመሸጥ ለጨረታ አቅርበውታል፡፡ ከብዙ የሽያጭ ድርድር በኋላ እንግሊዛዊ ቢሌኔር ሰር ጂም ራትክሊፍ 25 በመቶ የማንችስተር ዩናይትድን ድርሻ ገዝተዋል፡፡
የማንችስተር ዩናይትድ ቀንደኛ ደጋፊ እንደኾኑ የሚነገርላቸው ቢሌኔሩ ማንችስተርን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሱታል የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ እርሳቸውም ዋናው ዓላማዬ የማንችስተርን ኀያልነት መመለስ እና ከተቀናቃኞቹ በላይ ኾኖ እንዲቀመጥ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ለለውጥ ጅማሮ ይኾን ዘንድም ለውጦችን ጀምረዋል፡፡
በርካታ የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችም የክለቡን ኀያልነት እንደሚመልሱ ተስፋቸውን ጥለውባቸዋል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ አሁንም በሜዳ ላይ እያሳየው ባለው አቋም ትዕግሥት አጥተዋል ነው የተባለው፡፡ ከሻምፒዮን ሽፑ ኮቨንትሪ ጋር በእንግሊዝ ኤፍኤ ዋንጫ ለፍጻሜ ለማለፍ ባደረገው ጨዋታ ባሳየው አቋም የቡድኑ ደጋፊዎች ተበሳጭተዋል፡፡
ጨዋታውን በግዙፉ ዌንበለይ ስታዲዬም ተገኝተው የተመለከቱት ሰር ጂም ራትክሊፍ በቡድኑ ስለጀመረው ፕሮጄክት ተናግረዋል፡፡ “ደጋፊዎቹ ትዕግስት አጥተዋል፣ ለዛ ትንሽ አዝኛለሁ። ግን ጉዞ ነው ወደዱም ጠሉም ትንሽ መታገስ አለባቸው። ይህ የመብራት ማብሪያ ማጥፊያ አይደለም፤ እንደዚያ ማዞር አይችሉም” ማለታቸውን ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍብሪዚዬ ሮማኖ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ጨስፍሯል፡፡
አሠልጣኝ ኤርክ ቴን ሀንግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጫና እየበዛባቸው መጥቷል፡፡ ከጨዋታው በኋላ በትልቅ ደረጃ መጫዎት እንችላለን፤ ነገር ግን በተመሳሳይ ጨዋታ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ እንወርዳለን በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የአሠልጣኙ አስተያየትም ትችት እያመጣባቸው መኾኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ታሪካዊ ተጫዋች እና አምበል ሮይ ኪን ማንችስተር ዪናይትድ የቻምፒዮንስ ሽፕ ቡድን ይመስላል፤ ኮንቨንተሪ ደግሞ የፕሪሚዬር ሊግ ቡድን ይመስላል፣ ይህ ደግሞ በአሠልጣኙ ላይ የበለጠ ጫና እየፈጠረ ነው ሲል የቡድኑን ደካማ አቋም ተችቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!