ኢማኑኤል አሙኒኬ የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኾነ።

0
220

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኮትዲቯር ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ በፍጻሜ ጨዋታ በደረሰበት ሽንፈት ምክንያት አሠልጣኝ ጆሴ ፔሴሮ ከሥራ መልቀቁ ይታወሳል። ፌዴሬሽኑ ይህንኑ ተከትሎም ባወጣው የቅጥር ማስታዎቂያ መሰረት ስፔናዊው አሠልጣኝ ዶሜኔክ ቶርተር፣ ፖርቱጋላዊው አንቶኒዮ ኮንሴካዎ እና ናይጀሪያዊው ኢማኑኤል አሙኒኬ ተወዳድረዋል። በመጨረሻም አሙኒኬ ቡድኑን እንዲመራ ተመርጧል።

አሙኒኬ እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ1996 ኦሊምፒክ የናይጄሪያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ እርሱ የቡድኑ ምርጥ አጥቂ ነበር። ከ2008 እስከ 2023 በተለያዩ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኖች በአሠልጣኝነት የነበረው ቆይታም ጥሩ እንደነበር ተመስክሮለታል። በተለይ አሙኑኬ በ2019 የታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ በመኾን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ማድረጉ በስኬትነት ተጠቅሷል።

በመኾኑም የኢማኑኤል አሙኒኬ የሥራ እንቅስቃሴ ከተፎካካሪ አሠልጣኞች በልጦ በመገኘቱ እንዲመረጥ አድርጎታል ነው የተባለው። የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ሙሳ “ኢማኑኤል አሙኒኬ በተጫዋችነት፣ በአሠልጣኝነት እና በቡድን አማካሪነት የካበተ ልምድ ባለቤት ስለኾነ ጥሩ ብሔራዊ ቡድን ያዋቅራል ብለን ተስፋ አድርገናል። ሰለዚህ በየጨዋታዎች አሸናፊም ያደርገናል” ብለዋል።

የ53 ዓመቱ ኢማኑኤል ከ1991 እስከ 2004 በዛማሌክ፣ በስፖርቲንግ ሊዝበን፣ በባርሴሎና እንዲሁም በሌሎች ቡድኖች ተጫውቷል። የአሠልጣኝነት ሕይዎቱ ደግሞ 2008 መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here