“የትልቅ ጨዋታ ኮከቦች”

0
296

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ተጠናቀው የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ቡድኖች ተለይተዋል። ቡድኖቹ የተሻለ ኾኖ ቀጣዩን ዙር ለማለፍ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ የሳበ ተጋድሎ አድርገዋል።

ክለቦቹ ተመጣጣኝ ፍክክር በማሳየታቸውም በመጀመሪያው ዙር በሰፊ ግብ ያሸነፈ ወይም የተሸነፈ ቡድን አልነበረም። ይህ ማለት ቡድኖቹ ያደረጉት የመልስ ጨዋታ ወሳኝ እና ተጠባቂ ነበር። ባለፉት ሁለት ቀናት በተካሄዱት በእነዚህ የመልስ ጨዋታዎች ፒኤስጅ፣ ቦሩሲያዶርትሙንድ፣ ባየርሙኒክ እና ሪያልማድሪድ ተጋጣሚዎቻቸውን ረተው ግማሽ ፍጻሜ ደረሰዋል። ቡድኖቻቸው ለድል እንዲበቁ በተለየ በጨዋታው ምርጥ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችም የየጨዋታው ኮከብ ተብለው ተመርጠዋል።

የጀርመኑ ባየርሙኒክ ከሳምንት በፊት ወደ ለንደን ተጉዞ ከአርሰናል ጋር ሁለት አቻ ተለያይቶ ነበር። በመልሱ ጨዋታ ደግሞ በሜዳው 1 ለ 0 አሸንፏል። ይህ ውጤት ሙኒክን ለግማሽ ፍጻሜ እንዲበቃ አጎዞታል። በአውሮፓ እግር ኳስ መረጃ መሰረት በጨዋታው ከሁሉም ጎልቶ የታየው ጆሽዋ ኪሚች ነው። በቀኝ መስመር እና መሀል ላይ የሚጫወተው ኮሚች ከአርሰናል ጋር በነበረው የመልስ ጨዋታ የአርሰናልን የማጥቃት ሀይል በመግታት እና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ድንቅ ነበር ተብሏል።

ሪያልማድሪድ የአውሮፓ ኀያል መኾኑን አሳየ በተባለበት ጨዋታ ሲቲ በሜዳው እጅ ሲሰጥ የጨዋታው ኮከብ ኡራጋዊ ፍሬድሪኮ ቫልቨርዴ ነው። የሲቲ የመሀል ክፍል ኬቨን ደብሮይናን ጨምሮ ሮድሪን እና በርናንድ ሲልቫን የመሳሰሉ ኮከቦችን የያዘነው። ቫልቨርዴ ይህ የሲቲ የመሀል ክፍል ለአጥቂዎቹ ያለቀ ኳስ እንዳያቀብል እና ዘልቆም ግብ እንዳያስቆጥር ከአጋሮቹ የበለጠ ተመስጋኝ ኾኖ የጨዋታው ኮከብ ተብሏል።

በሜዳው ተሸንፎ አበቃለት የተባለው ፒኤስጅ ባርሴሎናን በሜዳው አሸንፎ አገግሟል። ለቡድኑ ውጤታማ መኾን ደግሞ ሁለት ግብ ካስቆጠረው ምባፔ በላይ የቀድሞው የካታላኑ ተጫዋች ኦስማን ደንበሌ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

እንደ ባርሴሎና ሁሉ የመጀመሪያውን የደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ የተሻለ የማለፍ እድል ነበረው አትሌትኮ ማድሪድ። ነገር ግን በመልሱ ጨዋታ የስፔኑ ክለብ ነገሮች ከብደውታል። ቦሩሲያዶርትሙንድ በድንቅ ደጋፊዎቹ ታግዞ ውጤቱን ቀልብሷል። በጨዋታው ድንቅ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከልም ጁሊያን ብራንዲት የጨዋታው ኮከብ ሽልማትን ወስዷል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here