ትኩረት ያገኙ የስምንተኛ ሳምንት መርኃ ግብሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።

0
245

ታኅሳሥ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።ባለፈው ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት ያስተናገዱት አፄዎቹ ከሽንፈት ለማገገም ሀድያን ይገጥማሉ።

አጼዎቹ በእስካሁን ጨዋታዎች በሁሉም ረገድ በጥሩ የመሻሻል ሂደት ውስጥ ነበሩ፡፡ በወላይታ በተሸነፉበት ጨዋታ ግን ከወትሮው በተለየ የተከላካይ ክፍላቸው ደካማ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዛሬው ጨዋታ የግብ እድል መፍጠሪያ አማራጮችን ማስፋት እና የተከላካይ መስመራቸውን አስተካክለው መግባት ይጠበቅባቸዋል።

አምስት ተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የፈጣን አጥቂያቸውን አቅም መጠቀም ከቻሉ የአጼዎቹን የግብ ክልል ማስጨነቃቸው አይቀርም እየተባለ ነው።

ፋሲል እና ሀድያ ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ፋሲል ከነማ በሁለት ጨዋታ አሸንፏል፡፡ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው ጨዋታዎች አጼዎቹ ስድስት ነብሮቹ ደግሞ ሦስት ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል። ምሽት 12ሰ ባሕርዳር ከነማ ድሬድዋ ከተማን የሚገጥምበት ጨዋታ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።

ድሬዎች በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የአማካይ ጥምረትና ያልተደራጀ የማጥቃት ክፍል ነበራቸው። ከአራተኛው ሳምንት በኋላ ግን መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል፡፡
በሊጉ ጅማሮ ጠንካራ የነበረውና በአራተኛው ሳምንት ጨዋታ በባንክ ተፈትኖ ሦስት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉም ከድክመቱ አገግሞ ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለሱም የድሬድዋ ጥንካሬ ነው።

በዛሬው ጨዋታ ከሊጉ አስፈሪ የማጥቃት ጥምረት አንዱ ከሆነው ከጣና ሞገዶቹ የአጥቂ ክፍል ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቀዋል ፡፡ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈው ነጥባቸውን አስራ አራት ያደረሱት የጣና ሞገዶቹ የሊጉን መሪዎች እግር በእግር መከታተላቸውን ቀጥለዋል።

ቡድኑ በሰባት ጨዋታዎች አስራ ሦስት ግቦች ያስመዘገበ ጠንካራ የማጥቃት ብቃት አለው። ቸርነት ጉግሳ ከጥሩ እንቅስቃሴ አልፎ በግቦች ተሳታፊ መኾን መጀመሩም የአጥቂ ጥምረቱን ይበልጥ አጠናክሮታል።

ሁለቱ ቡድኖቹ በስምንት ጨዋታ ተገናኝተው ባሕር ዳር አራት ጨዋታዎችን አሸንፏል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ያሸነፉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ቀን 9ሰ አትዮጵያ ንግድ ባንከ ከአትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ፡፡ 12ሰ ደግሞ ሀምበርቶ ከአትዮጵያ መድኅን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሁሉም ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል ሲል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሸር ካምኒ በድረ ገጹ አሳውቋል ፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here