ትናንት ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድን የሸኘው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬስ?!

0
445

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተሻለ ግማሽ ፍጻሜ የመድረስ እድል የነበራቸው የስፔኖቹ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ከውድድር ውጭ ኾነዋል። ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ ያገኘውን ድል በሜዳው ማስጠበቅ ተስኖት ለኪሊያን ምባፔው ፒኤስጅ እጅ ሰጥቷል።
በምሽቱ የኑካፕ ጨዋታ የ4 ለ 1 ሽንፈት ገጥሞታል። የፈረንሳዩ ክለብም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጀመሪያ ዙር ሽንፈት በኋላ ውጤት ቀልብሶ ማለፍ ችሏል።

በተመሳሳይ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሳምንት በፊት ዶርትሙንድን 2 ለ 1 አሸንፎ የማለፍ እድሉን አስፍቶ የነበረ ቢኾንም የትናንቱ ፈተና ከብዶታል። የ4 ለ 2 ሽንፈት አስተናግዶ በድምር ውጤት ከውድድር ውጭ ኾኗል።

ፒኤስጅ እና ዶርትሙንድ የግማሽ ፍጻሜ ቦታቸውን አረጋግጠዋል። ቀሪ ሁለቱ ቡድኖች ደግሞ ዛሬ ይለያሉ። ባየርሙኒክ ከአርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ከሪያልማድሪድ ከሳምንት የቀጠለው ፈተና ዛሬ መጨረሻውን ያገኛል። ሁለቱም ጨዋታዎች በግቦች ታጅበው አቻ መጠናቀቃቸው ይታወሳል።

የጀርመኑ ባየርሙኒክ ወደ ለንደን ተጉዞ ከአርሰናል ጋር ሁለት አቻ ተለያይቶ የዛሬውን ጨዋታ በሜዳው ያደርጋል። አርሰናል ከሻምፒዮንስ ሊጉ የአቻ ውጤት በኋላ በፕሪምየር ሊጉ መሸነፉ የተሻለ የተባለበትን የውድድር ዓመት እንዳያበላሸው ያሰጋል። አሠልጣኙ አርቴታ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ረስተን ታሪክ የምንሠራበትን እድል ዛሬ በአግባቡ መጠቀም አለብን የሚል ሀሳብ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሙኒኩ አጥቂ ሀሪኬን ለባየርሙኒክ ዓመቱን ያለዋንጫ ማጠናቀቅ ውድቀት ነው የሚል ሀሳብ ሰጥቷል። ቦንደስሊጋውን ከዓመታት በኋላ ያጣው እና ከጀርመን ዋንጫ በጊዜ የተሰናበተው የጀርመኑ ክለብ ብቸኛ ተስፋው ሻምፒዮንስ ሊጉ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ከሪያልማድሪድ በተመሳሳይ ዛሬ የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። ሲቲዎች ወደቤርናቦ ተጉዘው አቻ ውጤት ማስመዝገባቸው ለግማሽ ፍጻሜ መንገዳቸው መልካም ተብሏል። የዓምናው የዋንጫ ባለቤት ማንቸስተር ሲቲ የዛሬውን ጨዋታ በሜዳው በማድረጉም ወደቀጣዩ ዙር የማለፍ የተሻለ ግምት እንዳገኘ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።

የሲቲው አሠልጣኝ ጋርዲዮላ የቤትሥራችን አልጨረስንም፤ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ የተሻለ ፋላጎት ላይ እንገኛለን ብሏል። ከማድሪድ ጋር ብዙ ጊዜ ተጫዎቻለሁ አከብራቸዋለሁ ግን አልፈራቸው የሚል ሀሳብ ጨምሯል።

ትናንት ፒኤስጅን እና ዶርትሙንድን አራቱ ውስጥ ያስቀመጠው ሻምፒዮንስ ሊጉ ዛሬስ?! ምሽት አራት ሰዓት የሚጀምሩት ጨዋታዎች ምላሽ ይሰጣሉ።

ዘጋቢ:አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here