ከእግር ኳስ ውጭ ሌላ ሕይወት አስቤ አላውቅም” ጆርጂዮ ቺሊኒ

0
299

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጆርጂዮ ቺሊኒ ይባላል፤ ጣልያናዊ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ነው፡፡ ተጫዋቹ እግር ኳስን አኤአ በ1990 በሊቮርኖ ቡድን ጀምሮ በ2023 ሎስ አንጀለስን ጨምሮ በሰባት ክለቦች በመዘዋወር በ548 ጨዋታዎች ተሰልፎ 35 ግብ አስቆጥሯል፡፡

ቺሊኒ 18 ዓመት የሚጠጋ እድሜውን ያሳለፈው በጁቬንቱስ ክለብ ነው፡፡ በዚህ ክለብ ውስጥ አኤአ ከ2004 እስከ 2022 ድረስ በ561 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል፡፡ ከተከላካይ መሥመር እየተነሳም 27 ግብ በማስቆጠር ውጤታማ ኾኗል ሲል ሎስ አንጀለስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ተጫዋቹ አኤአ ከ2012 እስከ 2020 ዘጠኝ ተከታታይ የሴሪ ኤ ዋንጫዎችን ክለቡ እንዲያነሳ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።

ተጫዋቹ አምስት የሱፐር ኮፓ ኢታሊያ ድሎችን ከማጣጣሙ በተጨማሪ በርካታ ሽልማቶችን በግል አግኝቷል። በሴሪ ኤው ከአጠቃላይ ተጫዋቾች አምስት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ እና ሦስት ጊዜ ደግሞ በተከላካይ ዘርፍ “ምርጥ” ተብሎ ተመርጧል። ዘ ናሽናል ኒውስ ዶት ኮም እንደዘገበው ቺሊኒ እኤአ በ2015 እና በ2017 ክለቡን የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ እንዲደርስ የእሱ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡

በጣልያናዊ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ “ትልቅ ጎሬላ” እየተባለ የሚጠራው ጆርጂዮ ቺሊኒ ከሰሞኑ ራሱን ከእግር ኳስ ማግለሉን አስታውቋል።

የ39 ዓመቱ ቺሊኒ “በእግር ኳስ ጥሩ እና ጠንካራ ሕይወት አሳልፌአለሁ፡፡ ልዩ እና የማይረሳ ጊዜያትን ተጉዣለሁ፡፡ አሁን ግን አዲስ ምዕራፍን ለመጀመር ስል ራሴን ከእግር ኳስ ተጫዋችነት አግልያለሁ” ብሏል፡፡

“በእርግጠኝነት እግር ኳስ የወደፊት ሕይወቴም ነው፤ ከእግር ኳስ ውጭ ሌላ ሕይወት አስቤ አላውቅም “ብሏል፤ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ራሱን ቢያገልም ከስፖርት ዘርፍ እንደማይርቅ በመጠቆም፡፡

እግር ኳስ የሙሉ ጊዜ ሥራ ከመኾኑ በፊት እንደ አባቱ ሕክምና ማጥናት ይፈልግ የነበረው ቺሊኒ “ዩኒቨርሲቲ ስለመግባት እያሰብኩ ነው ያደግኩት” ብሏል። ለዚህም ራሴን ለማሻሻል በየቀኑ አዳዲስ እቅዶችን በመንደፍ ሕክምና ባላጠናም በሌሎች የትምህርት መስኮች ሐሳቤን ብሎም ፍላጎቴን አሳክቻለሁ ብሏል።

ጆርጂዮ ቺሊኒ የመጀመሪያ ዲግሪውን በምጣኔ ሃብት እና በንግድ አሥተዳደር ሁለት ዲግሪዎችን ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ደግሞ የማስተርስ ዲግሪውን እንደተቀበለ አውስቷል፡፡ ታዲያ በተማረባቸው የትምህርት መስኮች ራሱ በቀጥታ ገብቶ መሥራት ባይችልም ድርጅቶችን ከፍቶ ለሌሎች የሥራ እድል በመክፈቱ ደስተኛ ነው፡፡

ለጣልያን ብሔራዊ ቡድን 121 ጊዜ ተጫውቷል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ታሪክ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡”ጎሬላ” የሚል ቅጽል ስም የተቸረው ቺሊኒ ከ2008 እስከ 2010 ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የሴሪኤውን የዓመቱ ምርጥ የተከላካይ ተጫዋች ሽልማት ወስዷል ።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here