በጋና አክራ የአፍሪካ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል።

0
337

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል። የአፍሪካ ጨዋታዎች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና አክራ መካሄዱ ይታወቃል።
በውድድሩ ከ53 ሀገራት የተውጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያም በአምስት የኦሊምፒክ ውድድሮችና በአራቱ ኦሊምፒክ ያልኾኑ ስፖርቶች በድምሩ በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች መሳተፏ ይታወቃል። በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በውኃ ዋና፣ በጠረጴዛና ሜዳ ቴኒስ፣ በቦክስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ በ9 የወርቅ፣ 8 የብር እና 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች። ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 22 ሜዳሊያዎች 18ቱ የተገኙት በአትሌቲክስ ነው፤ 7 የወርቅ 7 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያ በአትሌቲክሱ ተገኝቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቦክስ ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ እንዲሁም በብስክሌት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በውድድሩ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክም ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ እንደሚገባ ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ልዑኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኀላፊዎች አቀባበል ያደርጉለታል ተብሎ ይጠበቃል።

በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ 101 ወርቅ 46 ብር 42 ነሐስ በድምሩ 189 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች። ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል።

በውድድሩ ከተሳተፉ 53 ሀገራት 45ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና እና ሞሮኮ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here