ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ሥራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል። በሚኒስቴሩ የስፖርት ፋሲሊቲ ልማት እና አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ አስማረ ግዛው ካፍ ባስቀመጠው መመዘኛ መሰረት የስታዲየሙ እድሳት እና ጥገና ሥራ መከናወን ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል።
በዚህም በመጀመሪያ ዙር እድሳት የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የተፈጥሮ ሳር ንጣፍ፣ የተመልካች መጸዳጃ ቤት፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍል እና የዳኞች ፣የፀረ አበረታች ቅመሞች ሕክምና ማዕከል ግንባታ መካሄዱን አመልክተዋል። በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ የተመልካቾች መቀመጫ፣ የመገናኛ ብዙኅን የሥራ ክፍል፣ የመብራቶች እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስክሪን የመትከል፣ የክብር እና ልዩ ክብር እንግዶች ፋሲሊቲዎች እንዲኹም ዘመናዊ የስታዲየም ውሃ ማጠጫ ሥርዓት የመዘርጋት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የምዕራፍ ሁለት እድሳት ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው ቀሪ ሥራዎች በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ብለዋል። ከእግር ኳስ ጋር ከተያያዙ የእድሳት ሥራዎች በተጨማሪ ነባሩን የአትሌቲክስ መሮጫ መም የመቀየር ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ መሙን ለመተካት የአስፋልት እና የጠረጋ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን፣ አጠቃላይ የመሮጫ መም እድሳት በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል። በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት በስታዲየሙ ይጀመራል ነው ያሉት።
በተያያዘም በምዕራፍ ሦስት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የበይነ መረብ የቲኬት ሽያጭ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የደህንነት ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች በስታዲየሙ እና ዙሪያው ያሉ የውጫዊ ገጽታ ሥራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል። ሥራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣ የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው የግንባታውን ከሦስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አመልክተዋል።
ካፍ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት የስታዲየሙ እድሳት መሟላት አለባቸው ያላቸው ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል። በሁለት ዙር ከሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች በተጨማሪ በምዕራፍ ሦስት ከስታዲየሙ ውጪ የሚሠሩ መሰረተ ልማቶች በካፍ መመዘኛዎች መሰረት ይገነባሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳት 47 ሚሊየን ብር እንዲኹም ለሁለተኛው ምዕራፍ 190 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን አመልክተዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ወይም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኀበር (ፊፋ) የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙ እድሳት ሥራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!