በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰከላ ወረዳ በመንግሥት እና በፕሮጀክት የታቀፉ በርካታ የአትሌቲክስ ክለቦች ይገኛሉ። እነዚህ ክለቦች በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አትሌቶችን እያፈሩ ይገኛሉ። በወረዳው ግሽዓባይ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ ውስጥ
አባል የኾኑት አትሌት አማኑኤል አደራው እና አትሌት አያሉ አስቻለው ሥልጠናዎችን አጠናክረው በመውሰድ በተለያዩ ውድድሮች እየተሳተፉ ናቸው። አትሌቶቹ ከዚህ በፊት በነበሩ የዞን እና የክልል ውድድሮች ውጤታማ ጊዜያትንም አሳልፈዋል። ቀጣይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች
በመሳተፍ ሀገርን ወክለው ለመሮጥ አልመው እየሠሩ መኾናቸውንም ነው ያስረዱት ። በተለይ በወረዳው በግንባታ ላይ ያለው የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ቢጠናቀቅ ደግሞ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ጠቁመዋል። የአካባቢው ሥነ ምኅዳር እና የመሬት አቀማመጥ
ለአትሌቲክስ ዘርፍ ምቹ በመኾኑ የበርካታ አትሌቶች መፍለቂያ መኾኑን የሰከላ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ እና የኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ አሠልጣኝ መልካሙ ጋሹ ገልጸዋል። የተጠናከረ ሥልጠና በመስጠት ሌሎች አትሌቶችን
ለማውጣት እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል። የሰከላ ወረዳ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ቢገባ ብቁ እና ተወዳዳሪ አትሌቶችን ለማውጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚወጣም አንስተዋል። ማዕከሉ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ባለድርሻ እና አጋር አካላት
የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የሰከላ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በ2009 ዓ.ም ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ ባለድርሻ አካላት እና አጋር አካላት ወጪ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየ ሲኾን በዚህ ዓመት አጋር እና
ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ቀሪ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በማሟላት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ዓለማየሁ አዳነ ገልጸዋል። ማዕከሉ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከተለያዩ አካባቢዎች አትሌቶችን መልምሎ በማሠልጠን
ዓለም አቀፍ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተስፋ ተጥሎበታል።
ዘጋቢ፦ ንጉስ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



