ድንቅ ምሽት ነበር ማንቸስተር ዩናይትድ ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመለሰ።

0
37
ኦልድ ትራፎርድ ደምቆ አመሸ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ከሮማ ጋር ባደረገው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በሁለት ግቦች ሲመራ ቆይቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባሳየው አስደናቂ ብቃት 3 ለ 2 በኾነ ውጤት አሸንፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በስድስት ደቂቃዎች ልዩነት ማቲያስ ሶውሌ እና ዶንየል ማሌን በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠሯቸው ግቦች ሮማን 2 ለ 0 መሪ አድርገው ነበር።
ይህን ተከትሎ በስቴዲየሙ የነበረው ድባብ የተቀየረ ሲኾን በሁኔታው ተበሳጭተው የነበሩ የዩናይትድ ደጋፊዎች የአረንጓዴ ቴኒስ ኳሶችን ወደ ሜዳ በመወርወር እንዲሁም አረንጓዴ እና ቢጫ ፊኛዎችን በመልቀቅ በክለቡ ባለቤቶች በግሌዘር ቤተሰቦች፣ በሰር ጂም ራትክሊፍ እና በክለቡ የእግር ኳስ ዳይሬክተር ጄሰን ዊልኮክስ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።
በተጨማሪም 70 ሚሊዮን ፓውንድ የወጣበት አማካዩ ካርሎስ ባሌባ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ መውጣቱ የክለቡን አሠልጣኝ ማይክል ካሪክን አበሳጭቶት ነበር።
ኾኖም በሁለተኛው አጋማሽ ማንቸስተር ዩናይትዶች ወደ ጨዋታው ተመለሱ ምሽቱንም አደመቁት የቡድኑ አንበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት በእርጋታ ወደ ግብነት ቀይሮ ልዩነቱን አጠበበ።
በዚህች ግብ የተነቃቃው ማንቸስተር ዩናይትድ ብሪያን ምቤሞ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ቢመለስም ኳሷን ያገኘው ማቴዎስ ኩኛ የሮማውን ተከላካይ ሊዮናርዶ ባሌርዲን ስህተት ተጠቅሞ ቡድኑን አቻ አደረገ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ኩኛ ድንቅ ግብ በማስቆጠር ዩናይትድን ለድል አበቃ።
በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ኩኛ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ዩናይትድ በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደደ ኾኖም ውጤቱ ሊቀየር አልቻለም በመጨረሻም የዩናይትድ አሸናፊነት ተበሰረ። ቡድኑም ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ የመጀመሪያ ድሉን አረጋገጠ።
በሌሎች ጨዋታዎች ደግሞ ባርሴሎና አስቶንቪላን 3 ለ 0፣ ፒኤስጂ ቪያሪልን 6 ለ 0፣ ባየር ሙኒክ አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 0 እንዲሁም ኢንተር ሚላን ፌይኖርድን 3 ለ 0 አሸንፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here