ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ውድድራቸውን እንዲያካሂዱ የዋግ ኽምራ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አሳሰበ።

0
235

ሰቆጣ: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)20ኛው የመላው ዋግ ባሕላዊ ስፖርት ውድድር እና 5ኛው የባሕል ፌስቲቫል በዝቋላ ወረዳ ጽጽቃ ከተማ ተጀምሯል።

በውድድሩም ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋግ ኽምራ ስር ኾነው የሚሳተፉት የኮረም ከተማ እና የወፍላ ወረዳን ጨምሮ ዘጠኝ ወረዳዎች በስምንት የስፖርት አይነቶች ይወዳደራሉ።

የዝቋላ ወረዳ ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የአሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታሁን አዱኛው የአንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የድሃና ወረዳ ባሕላዊ ስፖርት ተወዳዳሪ የዚህዓለም ተስፋው በቂ ዝግጅት ስለማድረጋቸው ተናግረዋል። በስፖርታዊ ጨዋነት እና ወንድማማችነትን በማጎልበት ለጥሩ ውጤት እንደሚፎካከሩ ተናግረዋል።

የጻግቭጂ ወረዳ ባሕላዊ ስፖርት ተወዳዳሪ ወጣት ሞገስ ጌታሁን የዝቋላ ወረዳ ሕዝብ ላደረገው አቀባበል እና መስተንግዶ አመሥግነዋል። ለዋንጫ እንደሚፎካከሩም ተናግረዋል።

የዝቋላ ወረዳ ሕዝብ ስፖርት ወዳድ እንደኾነ የወረዳው ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዝናቡ ሚካኤሌ ገልጸዋል፡፡ የተለመደው ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ኀላፊው የኮረም እና የወፍላ ተወዳዳሪዎችን በማበረታታት ወደ ቀደመ ቤታቸው እንደመጡ እንዲሰማቸው ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሰሎሞን አስፋው ስፖርት የሚጠይቀው ወንድማማችነትን እና ሰላምን እንደኾነ አስገንዝበዋል።

የውድድሩ ዓላማ የባሕል ስፖርቱን በማሳደግ ዋግን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መመልመል ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን ለኹሉም ተወዳዳሪዎች መልካም ውጤት እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።

የባሕል ስፖርት ውድድሩም ከመጋቢት 8/2016 ዓ.ም እስከ መጋቢት 15/2016 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ነው ተብሏል፡፡ በውድድሩም ከ500 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

በመክፈቻ መርሐ ግብሩም ድሃና ወረዳ ጻግቭጂ ወረዳን በወንዶች የ”ገና” ጨዋታ 1 ለ 0 ሲያሸንፍ፤ አስተናጋጁ ዝቋላ ወረዳ ከሰቆጣ ዙርያ ጋር አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here