“የአጼዎቹ የፕሪምየር ሊግ ጉዞ ሲፈተሽ”

0
10913

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ እግር ኳስ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለውጥ ካሳዩ ክለቦች መካከል ፋሲል ከነማ አንዱ ነው። ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ የተሻለ ተፎካካሪ ኾኗል። የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካነሱ ጥቂት የክልል ክለቦች ውስጥም ስሙን በታሪክ አስቀምጧል።

ፋሲል የተመሰረተው በ1960 ዓ.ም ነው። ቡድኑ 20 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለውን የፋሲለደስ ስታዲየም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስሙ ማስመዝገቡን ከይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ያገኘነው ማስረጃ ይጠቁማል።

ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ በመጫወት ልምድ እና ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች አሰባስቧል። እስከ 18ተኛ ሳምንት ድረስ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥብ አንሶ ይገኛል። ቡድኑ ከሰበሰባቸው ተጫዋቾች ልምድ እና ጥራት አኳያ ያለበት ደረጃ በቂ ነው ባይባል በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ግን ይገኛል።

የፋሲልን 14 ጨዋታዎች በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የተከታተሉት የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ከ17 ዓመት በታች የወጣቶች እግር ኳስ አሠልጣኝ ኤልያስ መኮንን ፋሲል ከነማ በሀገሪቱ ካሉ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል “በእኔ አተያይ በኹሉም መመዘኛ ጠንካራው ቡድን ነው፤ የቡድኑ የፊት መስመር ተጫዋቾች በቴክኒክም በታክቲክም ብቃታቸው ከፍ ያለ ነው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋቾች አማኑኤል ፣ ጋቶች እና ሌሎች የተሻሉ ተጫዋቾች የሚገኙት ፋሲል ከነማ ቡድን ውስጥ እንደኾነ አስታውሰው ለጥንካሬው ቀዳሚ ምክኒያት ብለውታል።

ባለሙያው የፋሲል የመስመር እና የፊት አጥቂዎች ኳስን ይዘው ቢጫወቱም ከልክ በላይ በራስ የመተማመን ስሜት የማንጸባረቅ ውስንነት ይስተዋልባቸዋል፤ ይህም ‘በእኔ ግምገማ’ ቡድኑ ነጥብ እንዲጥል አድርጎታል ብለዋል።

የቡድኑ አሠልጣኞች በትጋት በመሥራታቸው መሰል ውስንነቶችን ከጨዋታ ጨዋታ በማሻሻል ወደ አሸናፊነት መምጣት ጀምሯል እንጅ አጀማመሩ እና አካሄዱ መልካም የሚባል አልነበረም ሲልም ሀሳባቸውን ጨምረዋል።

ባለሙያው በመጀመሪያው የውድድር ዙር የፋሲል ቋሚ ተሰላፊዎች ጠንካራ ቢኾኑም አጥቂዎቹ በቡድን አጥቅተው ቡድናዊ ውጤት ከማስመዝገብ ይልቅ የግል ብቃታቸውን ብቻ ለማሳየት ያደርጉት የነበረው “ራስን የማሳየት” ጉጉት ቡድኑን ለተደጋጋሚ ሽንፈት እንደዳረገው ባለሙያው አስታውሰዋል።

ጠንካራው የፋሲል ከነማ የተከላካይ ክፍል በመጀመሪያው ዙር ከግብ ተባቂ ጀምሮ የቆመን ኳስ መስርቶ ከመጫወት ይልቅ በረዥም አሻምቶ ግብ ለማስቆጠር የሚደረግ ልምምድ ይደጋገም ነበር። ይህ ደግሞ የተቃራኒ ተጫዋቾች ኳስ የማግኘት እድላቸው 50 በመቶ ነው። በሌላ አገላለጽ የፋሲል የተከላካይ ክፍል ከዘመናዊ እግር ኳስ አጨዋወት ወጥቶ ኳስን በማሻማት የሚደረግ የአጨዋወት ስልት መከተሉ ጎድቶታል ለማለት እደፍራለሁ ብለዋል።

ታዋቂው የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኝ ዮናስ አዘዘ በበኩሉ ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ ሁሉንም ቡድን ያሸነፉ በተጨማሪም በውጭ ሀገር በመጫወት ልምድ እና ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች ያሠባሠበ ጠንካራ ቡድን ነው ይላል። “ፋሲል ከነማ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ነው የሚመስለው” ያሉት የእግር ኳስ ተንታኙ ፤ ጌታነህ፣ ጋቶች፣ አማኑኤል እና ምኞትን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በመያዙ ጥቃቅን ስህተቶችን ካረመ ተጽዕኖን ፈጥሮ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የሚችል ቡድን ነውም ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኙ ዮናስ አክሎም የቡድኑ መሪዎች ዓላማ የወደፊት ጠንካራ ቡድን መገንባት ሳይኾን በዚህ ዓመት ዋንጫ ለመውሰድ ይመስላል ብሏል። ነገር ግን ቡድኑ በተገለጸው ልክ እየተጓዘ አይደለም።

ስለዚህ ቡድኑ ከመሪው ክለብ ያለው የነጥብ ልዩነት ጠባብ በመኾኑ እና በርካታ ቀሪ ጨዋታዎች ስላሉት ሁሉም ተጫዋቾች በልካቸው ከተጫወቱ ሻምፒዮን የማይኾኑበት ምክንያት የለም ሲል ሀሳቡን አክሏል።

የፋሲል ከነማ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው “አንደኛውን ዙር ካጠናቀቅን በኋላ ያሉብንን ድክመቶች እና ጥንካሬዎች ለመለየት ተሞክሯል” ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ የነበሩትን ክፍተቶች ለመሙላት እንዲኹም የታዩ ጉድለቶችን በማስተካከል በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ የተቻለውን ኹሉ እንደሚያደርጉ አስገንዝበዋል።

“በየጨዋታውም ግብ ላይ የመድረስ ችግርን አሻሽለናል፤ ነገር ግን የምናገኛቸውን እድሎች ወደ ግብ የመቀየር ችግር አለብን። ለዚህም ነው ብዙ ግብ ያላስቆጠርነው” ብለዋል።
በመኾኑም የቡድኑን ውስንነቶች በሥራ በማስተካከል ከቀን ቀን የተሻሻለ ጠንካራ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ጥረት እያደረጉ እንደኾነ አስገንዝበዋል።“ከሥራችን ተነስተንም የሁለተኛውን ዙር ውስን ጨዋታ ስንገመግመው እስከ መጨረሻው የዋንጫ ፉክክር እንደምንቆይ ተስፋ አለን” ብለዋል።

አሠልጣኙ አክለውም የአማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ወደ አሜሪካ መሄድ በቡድኑ ውስጥ ክፍተት እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ኾኖም እንደ ሀገር ያለውን ጠቀሜታ በማመን ለሌሎችም የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ይዞት የመጣውን ተስፋ በመገንዘብ ዝውውሩ እንዲጠናቀቅ ስለመደረጉም አስረድተዋል። በቦታውም የሚመጥኑ ወጣት ተጫዋቾችን በመመደብ ውጤታማ እየኾኑ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here