ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ተኛ ሳምንት መርሐ ግብሮች ትናንት ጀምረው እየተካሄዱ ነው። ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲኾን የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ከመቻል የሚያካሂዱት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪምየር ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት መልካም ጊዜን እያሳለፈ ነው። በ17 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ 36 ነጥቦችን በመሠብሠብም ሊጉን እየመራ ነው።
መቻሎችም በዚህ የውድድር ዘመን የተሻለ እንቅስቃሴን እያሳዩ ነው። ሊጉን መምራት የቻሉባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መቀዛቀዝ አሳይተዋል። በደረጃ ሰንጠረዡም በንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተበልጠው በ33 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ምሽት አንድ ሰዓት በሚጀመረው በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች አሸንፎ ለዋንጫው ይበልጥ ተፎካካሪ ለመኾን ብርቱ ትግል እንደሚያደርጉ ይታመናል። ብሩክ እንዳለ እና ፉአድ ፈረጃ በንግድ በኩል በጉዳት ጨዋታው ሊያመልጣቸው እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል። በመቻል በኩል ደግሞ አስቻለው ታመነ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ መኾኑ ተረጋግጧል።
ቀን 10 ሰዓት በሚጀምር ጨዋታ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ሦስት ብቻ ነው። ድሬዳዋ በቅርብ ጨዋታዎች መሻሻሎችን እያሳዩ መጥተዋል። በደረጃ ሰንጠረዡም በ25 ነጥብ ሰባተኛ ናቸው። ሀዋሳዎቹ ደግሞ በ22 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ኾነው ነው የዛሬውን ጨዋታ የሚያከናውኑት።
ዘጋቢ: አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!