“የካርድ ቀበኛው” ሰርጆ ራሞስ

0
273

ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእግር ኳስ ሕይወቱ ያላሳካው ድል የለም። የስፔን ላሊጋ፣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ እና ሌሎች ዋንጫዎች በሪያል ማድሪድ አሳክቷል። ወደ ፈረንሳይ ተጉዞም የፈረንሳይ ሊግ አንድ ዋንጫን ተቋድሷል።

ሀገሩ ስፔን በዓለም እና በአውሮፓ ዋንጫ ስትደምቅም የወርቃማው ትውልድ ፊታውራሪ ነበር – ሰርጆ ራሞስ። በእግር ኳስ ከታዩ ምርጥ ተከላካዮች መካከል አንዱ መኾኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

እንዲህ በስኬቱ የሚቀናበት ስፔናዊ ተከላካይ የባሕሪው ነገር ከስኬቱ በተቃራኒ የሚነገር ነው። ተጫዋቹ ሜዳ ላይ ከሚያሳየው ምርጥ ብቃት ባልተናነሰ በአምባጓሮ እና ጸብ አጫሪነቱም ይታወቃል። ይሔ ቁጡ ባሕሪው በተደጋጋሚ የካርድ ሰለባ አድርጎታል።

ከሰሞኑ በስፔን ላሊጋ ሲቪያ በሪያል ሶሲዳድ ሲሸነፉ አንጋፋው ተከላካይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህም ራሞስ እስካሁን በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበትን አጋጣሚ 29 አድርሶታል።

ራሞስ ድንቅ አሻራ ባሳረፈበት ሪያል ማድሪድ 26 ጊዜ፣ በፒኤስጂ ሁለት ጊዜ እና በሲቪያ አንድ ጊዜ ነው ቀይ ካርድ የተመለከተው።

“ጊቭ ሚ ማይ ፉትቦል” የተሰኘ የመረጃ ምንጭ እንደሚለው ስፔናዊው ተከላካይ ብዙ ቀይ ካርድ በማየት በዓለም 48 ቀይ ካርድ ካየው ከጀራርዶ ቤዶያ ቀጥሎ ሁለተኛው ቀዳሚ ተጫዋች ነው። በዚህም “የካርድ ቀበኛ” የሚል ቅጽል ስም አግኝቷል።

ለስፔን ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገው እና ትልልቅ ክብሮችን ያገኘው ራሞስ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ቀይ ካርድ አይቶ አለማወቁ አስገራሚ መኾኑን መረጃው አስነብቧል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here