“የመጨረሻው ፈንጠዝያ” የማን ይኾን?!

0
464

ባሕርዳር: መጋቢት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው ዓለም ተወዳጅ እንደኾነ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ከሌሎች ሊጎች በተሻለ ተፎካካሪነት የሚታይበት መኾኑ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ከሌሎች ምክኒያቶች ጋር ይጠቀሳል።

በስፔን፣ ጣሊያን እና ጀርመን በመሳሰሉ ትልልቅ በሚባሉ ሊጎች በየዓመቱ መጨረሻ ዋንጫ የሚያነሱ ቡድኖች ከተከታዮቻቸው የሚያስመዘግቡት ልዩነት የሰፋ ኾኖ ይታያል። እንደ ጎል ዘገባ እነዚህ ሊጎች ዘንድሮ እንኳ ገና ብዙ ጨዋታዎች እየቀሩ በየሊጉ የዋንጫ ባለቤት የሚኾነውን ቡድን ለመገመት ከባድ አይደለም።

በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ከታሪካዊ ተቀናቃኙም ይኹን ከከተማ ተፎካካሪው አትሌቲኮ ማድሪድ በበቂ ልዩነት ተቀምጧል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው” ክስተቱ” ጅሮናም ቢኾን ለነጮቹ ስጋት የመኾን ከዚህ በላይ አቅም የለውም እየተባለ ነው። በጀርመን ባየር ሊቨርኩሰን፣ በጣሊያን ኢንተር ሚላን በውድድር ዓመቱ የየሊጋቸው አሸናፊ እንደሚኾኑ መገመት ብዙ ስህተት ላይ አይጥልም።

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ግን ዋንጫ እንዲህ እንደዋዛ አይገኝም። ሁለት ፣ ሦስት ቡድኖች በየዓመቱ ዋንጫውን ለማንሳት አስከመጨረሻዎቹ ሳምንታት ብርቱ ትግል ያደርጋሉ። ባለፉት ዓመታት ዋንጫውን በተከታታይ የጋርዲዮላው ሲቲ ያንሳ እንጅ እንደሌሎች ሊጎች በሰፊ የነጥብ ልዩነት ግን አይደለም።

በ2021/22 የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲ የዋንጫ ባለቤት ሲኾን ሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ አንሶ ነው የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው። የዋንጫ ባለቤቱን ለመለየትም የመጨረሻውን ጨዋታ የመጨረሻ ፊሽካ መጠበቅ ግድ ነበር።

በ2022/2023 የውድድር ዘመን ደግሞ የጋርዲዮላው ቡድን ፈተና አርሰናል ነበር። አብዛኛውን የውድድሩን ጊዜ የሊጉ አናት ላይ የነበረው የአርቴታው ቡድን መንገድ ላይ የጣላቸው ነጥቦች በመጨረሻ ዋጋ ቢያስከፍለውም የሊጉ ፉክክር የጠነከረ እንዲኾን ግን ባለውለታ ነው። የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅም ከሲቲ በአምስት ነጥብ አንሶ ነው የጨረሰው። ይህ ማለት የሊጉ አንድ ጨዋታ አስኪቀር ድረስ የዋንጫው ባለቤት አልተለየም ነበር ማለት ነው።

የፕሪምየር ሊጉ የዚህ የውድድር ዘመን ፉክክር ደግሞ ይበልጥ ጠንክሮ ሦስት ቡድኖችን አፋጧል። 27 ሳምንታትን በተጓዘው የሊጉ ጉዞ አርሰናል 64 ነጥቦችን ሰብስቦ ሊጉን እየመራ ነው። በግብ ልዩነት የተበለጠው ሊቨርፑል እና በአንድ ነጥብ ዝቅ ያለው ማንቸስተር ሲቲ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።

10 ጨዋታዎች በቀሩበት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ማን ያነሳል የሚለው አሁን ትልቅ አጀንዳ ኾኗል። ፍንጭ ይሰጣል የተባለው የሊቨርፑል እና የማንቸስተር ሲቲ ጨዋታም አቻ ተጠናቆ ሦስቱን ቡድኖች ይበልጥ በነጥብ እንዲቀራረቡ አድርጓል።

ሱፐር ስፓርት የመረጃ ምንጭ ከየካቲት ወር በፊት ሦስቱ ቡድኖች በነበራቸው አቋም ሲቲ እና ሊቨርፑል ቀዳሚ የዋንጫ ተገማች ነበሩ ይላል። አሁን ላይ ግን አርሰናልን አቅሎ ማየት ስህተት ነው እንደዘገባው ሀተታ።

የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ከገባ አርሰናል ስምንት የፕሪሜየር ሊግ ጨዋታዎችን አድርጎ ሁሉንም አሸንፏል። በእነዚህ ጨዋታዎች ቡድኑ 33 ግቦችን ማስቆጠሩ ደግሞ የለንደኑን ክለብ የስኬት ተገማችነት ከፍ ያደርገዋል።

የሦስቱ ቡድን ቀጣይ ተጋጣሚዎች ጥንካሬ በዋንጫው የመጨረሻ መዳረሻ ላይ ወሳኝ ናቸው። ዘኢንዲፔንዳንት እንደሚለው ሦስቱ ቡድኖች በተለይ ከሜዳቸው ውጭ የሚያስመዘግቡት ውጤት በዓመቱ መጨረሻ ለሚሰበስቡት ፍሬ ወሳኝ ነው።

በዚህ መሰረት አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ሲቲ ከቀሪ 10 የሊጉ ጨዋታዎች አምስቱን በሜዳቸው፣ አምስቱን ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ ያደርጋሉ። የፕሪምየር ሊጉ መሪ አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ፣ ብራይተን፣ ቶትንሃም ፣ዎልቭስ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ከሜዳው ውጭ ይገጥማል።

ሊቨርፑል ከሜዳው ውጭ የሚገጥማቸው ቡድኖች ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ፉልሃም፣ ዌስትሀም፣ ዎልቭስ እና አስቶን ቪላ ናቸው። ክርስቲያል ፓላስ፣ ቶትንሃም፣ ፉልሀም፣ ብራይተን እና ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ የጋርዲዮላው ቡድን ከሜዳ ውጭ ፈተናዎች ናቸው።

እነዚህ ጨዋታዎች ቡድኖች በሜዳቸው ከሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በበለጠ እንደሚፈትኗቸው ይታመናል። በተጨማሪም የተጫዋቾቻቸው ከጉዳት እና ቅጣት መራቅ ለቡድኖቹ የመጨረሻ ውጤት ማማር ወይም በተቃራኒው ለመኾን ወሳኝነት አለው።

ለጊዜው በአርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ሲቲ መካከል ያለው ልዩነት የአንድ ነጥብ ብቻ ነው። የእግር ኳስ አፍቃሪያንም የየራሳቸውን ማሳመኛ ነጥብ በማንሳት ለዋንጫው ግምታቸውን እየሰጡ ነው። ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ የመጨረሻው ፈንጠዝያ የማን ይኾን? የሚለው ነው፡፡

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here