“አፍሪካውያን የሚደምቁበት” የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች

0
456

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1965 ነው። ሃሳቡ ግን ከዚህም በላይ ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል የመላ አፍሪካ ጨዋታ።

በ1920ዎቹ አፍሪካውያን በስፓርት ለመወዳደር እና አንድነታቸውን ለማጠናከር በሃሳብ ተስማምተው ውድድሮችን ለማዘጋጀት በአልጀሪያ እና ግብጽ ሙከራ ተደርጎ ሁለቱም አልተሳካም።
ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ይዘው ልጆቿን ለመከራ ሃብቷን ለምዝበራ የዳረጉት አውሮፓውያን ናቸው። የአፍሪካውያን በአንድ መሰባሰብ ለረገጧቸው አፍሪካውያን የነጻነት መንገድ ምክንያት እንዳይኾን በመስጋት ውድድሩ እውን እንዳይኾን አድርገዋል።

አንደ ኦድስ ፒድያ ዘገባ ከታሰበ ዓመታትን ያስቆጠረው ይሄው የመላ አፍሪካ ጨዋታ በ1965 በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አውቅና አግኝቷል። የመጀመሪያው ውድድርም ኮንጎ ብራዛቪል ላይ ተከናወነ። ጊዜው ብዙ አፍሪካውያን ብዙ ነገር ካሳጣቸው የቅኝ ግዛት ቀንበር እየወጡ የነበረበት ጊዜም ነበር።

እንዲህ የተጀመረው የመላ አፍሪካ ጨዋታ አሁን በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ደማቅ ውድድር ኾኗል። የዘንድሮውን ውድድርም ጋና እያስተናገደችው ነው።ውድድሩን ያዘጋጁት የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር እና ከአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ጋር በመተባበር ነው።

በ30 የውድድር ዓይነቶች አምስት ሺህ ስፖርተኞች ለሜዳሊያ ይፎካከራሉ። ከ30ዎቹ ውድድሮች የብስክሌት፣ የሜዳ እና የጠረንጴዛ ቴንስ፣ ዋናን ጨምሮ በስምንት የውድድር ዓይነቶች የኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚረጋገጠው በዚሁ ውድድር በሚመዘገብ ውጤት ነው። ትልልቅ የአፍሪካ ስፖርተኞች በዚህ ውድድር የሚሳተፉበት በመኾኑ ለውድድሩም ድምቀት ይሰጠዋል።

ነገር ግን በጋናው ድግስ ትልልቅ ተወዳዳሪዎች አይካፈሉም። ምክንያት የተባለው ደግሞ የፓሪሱ ኦሎምፒክ ሊጀመር የወራት እድሜ ብቻ መቅረቱ ነው። በተለይ አትሌቶች ከድካም እና ጉዳት ለመራቅ በውድድሩ ከመሳተፍ ተቆጥበዋል። ውድድሩ መካሄድ የነበረበት ባለፈው ነሐሴ ወር የነበረ ቢኾንም በገንዘብ እና መሰል ችግሮች መገፋቱ ይታወሳል።

ጋና ለውድድሩ ትልቅ ዝግጅት አድርጋለች ተብሏል። 145 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሁለገብ የውድድር ሜዳ ተሠርቶ ዝግጁ ኾኗል። አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ እና ራግቢን የመሳሰሉ ውድድሮች የሚካሄዱበት የዩኒቨርሲቲ ጋና ሜዳም ብዙ ተደክሞበታል። የሀገቱ ትልልቅ ከተሞች አክራ፣ ኩማሲ እና ኬፕ ኮስትም በእንግዶች ደምቀዋል።

ኢትዮጵያም በውድድሩ በዘጠኝ ስፖርቶች 149 ስፖርተኞች የምታሳትፍ ሲሆን ከነዚህም አምስቱ የኦሊምፒክ ውድድሮች እና አራቱ የኦሊምፒክ ውድድር ያልሆኑ ስፖርቶች ናቸው።
አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውኃ ዋና፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌት እና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የውድድር ዓይነቶች ናቸው።

ዝላይ እና ዲስከስ ውርወራ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከምትሳተፍባቸው የውድድር ዓይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ።በአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተለያዩ ዙሮች ተከፋፍሎ ጋና መግባቱን ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ: በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here