“የታላላቆቹ ምርጫ” ዣቪ አሎንሶ

0
437

ባሕርዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስፔናዊ አሠልጣኝ አሎንሶ በተጫዋችነት በሊቨርፑል፣ ሪያል ማድሪድ እና ባየርሙኒክ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፤ ትልልቅ ዋንጫዎችንም አንስቷል።

ሁለት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ እና ከስፔን ጋር ያሳካው የዓለም ዋንጫ ደግሞ በተጫዋችነት ያገኛቸው ትልልቅ ክብሮቹ ናቸው። በተጫዋችነት ዘመኑ በመሀል ሜዳ ምሳሌ ተደርገው ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ነው።

ከተጫዋችነት በተጨማሪ አሎንሶ አኹን በአሠልጣኝነትም እየተወደሰ ነው። የጀርመኑን ባየርሊቨርኩሰን እየመራ ሳይጠበቅ ለቦንደስሊጋው ዋንጫ እየተቃረበ ነው። ቀድሞውኑ በባየር ሙኒክ የበላይነት በሚጠናቀቀው ሊግ ዘንድሮ ይህ የሚሳካ አይመስልም። 24 ሳምንታትን በተጓዘው ቡንደስ ሊጋ ባየር ሊቨርኩሰን ሙኒክን በ 10 ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው። ክለቡ በዩሮፓ ሊግም ምርጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

ሊቨርኩሰንን እንዲህ ለትልቅ ክብር እያንደረደረ ያለው ስፔናዊ አሎንሶ ብዙ ሙገሳ እና አድናቆት እየተቸረው ነው። በቀጣይ በትልልቅ ክለቦች የሚታይ ትልቅ አሠልጣኝ አንደሚኾንም ተገምቷል።

ይህን ተከትሎ ትልልቅ ክለቦች አሎንሶን አሠልጣኛቸው ለማድረግ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ማላይ ሜል አንዳስነበበው በተለይ ሊቨርፑል እና ባየር ሙኒክ ስፔናዊ አሠልጣኝ ለመቅጠር ሩጫ ላይ ናቸው። በሊቨርፑል እና ባየርሙኒክ ተጫውቶ ያሳለፈው ይህ አሠልጣኝ ቀጣይ ዓመት ከሁለቱ በአንዱ ክለብ መገኘቱ የማይቀር ሀቅ ኾኗል።

ሊቨርፑል ከውጤታማው አሠልጣኙ የርገን ክሎፕ ጋር በመጭው ክረምት ይለያያል። በእግራቸው የሚተካ ኹነኛ አሠልጣኝም ክለቡ ይፈልጋል። የመጀመሪያ ምርጫ ደግሞ አሎንሶን አድርጓል።

ባየርሙኒክ በቡንደስ ሊጋው ዋንጫውን ለማጣት ተቃርቧል። በጀርመን ዋንጫም ከውድድር ውጭ ነው። በዚህም ምክንያት አሠልጣኙ ቶማስ ቱሸል የጊዜ ጉዳይ ካልኾነ በመንበራቸው ብዙ ርቀት አይጓዙም እየተባለ ነው። ተተኪያቸው ደግሞ አሎንሶ እንዲኾን የክለቡ አመራሮች ፍላጎት ነው።

በብዙ ምርጥ አሠልጣኞች ስር መሠልጠኑ ለአኹኑ የአሠልጣኝነት መልካም ጅማሮ ትልቅ እድል ነው የሚለው አሎንሶ ምርጫው የት አንደኾነ ፍንጭ አልሰጠም። ካርሎ አንቾሎቲ ፣ ጆዜ ሞሪንኾ እና ፔፕ ጋርዲዮላ አሎንሶን በተጫዋችነት ካሠለጠኑ ትልልቅ አሠልጣኞች መካከል ናቸው። ከእነዚህ አሠልጣኞች ሰለተማረው ነገር የተጠየቀው ስፔናዊው አሠልጣኝ “ውሳኔዎችን እንዴት እንደሚያሳልፉ በቅርበት ተከታትያለሁ፤ ነገርግን ሁሉንም ነገር አትወሰድም የራስህን መንገድ ትፈጥራለህ እንጅ” ሲል መልሷል።

በዋናነት የአንቾሎቲን እና የጋርዲዮላን የአሠልጣኝነት ጥበብ በሚጠቅመው መንገድ እንደወሰደ የሚነገርለት አሎንሶ በባየር ሊቨርኩሰን አስገራሚ ሥራ እየሠራ ቢኾንም ብዙ ግን የሚቆይ አይመስል። ጥያቄው ቀጣይ ማረፊያው የት ነው? አንፊልድ!? ወይስ አሊያንዝ አሪና!? የሚለው ነው።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here