የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደተዘጋጁ የወሎ ኮምቦልቻ እግርኳስ ክለብ ተጫዋቾች ተናገሩ።

0
251

ኮምቦልቻ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የክለቡ ተጫዋቾች አምበሉ ቃለፍቅር መስፍን እና የመሀል ሜዳ ተጫዋች ሄኖክ ከበደ በመጀመሪያ ዙር የከፍተኛ ሊግ ውድድር የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ዘግይተው በመጀመራቸው የተሻለ ውጤት አለማስመዝገባቸውን ነው የገለጹት።

ከተማ አሥተዳደሩ ለክለቡ የሚችለውን ያሕል ድጋፍ እያደረገ ቢኾንም የተጨዋቾች ደመወዝ በመዘግየቱ እንዲስተካከል ተጨዋቾቹ ጥያቄ አቅርበዋል። በሁለተኛው ዙር ክለቡ በተሻለ ውጤት እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት ።

የወሎ ኮምቦልቻ እግርኳስ ክለብን ከተረከቡ ገና ሁለት ወር ያልሞላቸው አሠልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ሊግ ውድድር ክለቡን ከወራጅ ቀጠና አውጥተው የተሻለ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለክለቡ ውጤት መሻሻል የከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን የተናገሩት አሠልጣኙ ለተጫዋቾች ያልተከፈለ ቀሪ ደመወዝ በመክፈል ተጫዋቾችን ማበረታታት እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አስቻለው ብርሃኑ በበኩላቸው ለክለቡ ተጫዋቾች ያልተከፈለ ደመወዝ በአጭር ጊዜ እንዲከፈል ከተማ አሥተዳደሩ ጋር የተግባቡ መኾኑን ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ለሁለተኛ ዙር የክለቡ ውጤታማነት የበጀት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን እና በጀት መጽደቁን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር ደካማ ውጤት በመመዝገቡ ከአሠልጣኙ ጋር በስምምነት በመለያየት አዲስ አሠልጣኝ ማስፈረማቸውን እና በሁለተኛው ዙር የተሻለ ውጤት ለማምጣት በመጀመሪያው ዙር ጥሩ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።

ወሎ ኮምቦልቻ እግርኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ እየተወዳደረ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ከ13 ጨዋታዎች 11 ነጥብ በመሰብሰብ በወራጅ ቀጠና 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዘጋቢ:- ከድር አሊ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here