አዲስ አበባ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በስኮትላንድ ግላስኮው በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቀባበል ተደርጎለታል።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 13 አትሌቶችን ያሳተፈችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ አምስተኛ በመሆን ውድድሯን ማጠናቀቋ ይታወሳል ።
ልዑኩ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ወደ ሀገሩ የተመለሰ ሲኾን የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በቦሌ ኤርፖርት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
በስኮትላንድ ግላስኮው በተካሄደው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌት ፅጌ ዱጉማ በ800 ሜትር እና ፍሬወይኒ ኃይሉ በ1500 ሜትር ለኢትዮጵያ ወርቅ ማስገኘት ችለዋል።
በሴቶች 3000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ ብር ያስገኘች ሲኾን በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት መኾን ችሏል። ለልዑኩ ከተደረገለት አቀባበል በኋላ ደግሞ የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር የሚደረግ ይኾናል።
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!